እስካሁን ከ28 ሚሊየን በላይ መራጮች የምርጫ ካርድ ወስደዋል - ኢዜአ አማርኛ
እስካሁን ከ28 ሚሊየን በላይ መራጮች የምርጫ ካርድ ወስደዋል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2018 (ኢዜአ)፦ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ እስከ መጋቢት 18 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ከ28 ሚሊየን በላይ መራጮች የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የተለያዩ የቅድመ-ምርጫ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑ ይታወቃል።
ምርጫ ቦርድ እስከ መጋቢት 18 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ 28 ሚሊዮን 365 ሺህ 310 መራጮች መመዝገባቸውን አስታውቋል።
ከነዚህም 15 ሚሊዮን 317 ሺህ 567 ወንዶች እና 13 ሚሊዮን 47 ሺህ 743 ሴቶች ናቸው።
በተያያዘም ቦርዱ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ እንዲያደርጉባቸው የተመደቡ የሕዝብ እና የንግድ መገናኛ ብዙኃን ብዛትን ይፋ አድርጓል።
ጠቅላላ የመገናኛ ብዙኃን ብዛት 50 ሲሆን ሬዲዮ 24፣ ቴሌቪዥን 20 ጋዜጦች 6 መሆናቸውን ቦርዱ አመልክቷል።