ለቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ክለብ የ100 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ለቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ክለብ የ100 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተደረገ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2018(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እና ቢጂአይ ኢትዮጵያ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ክለብ የ100 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረጉ።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ክለብ ከገጠመው የመፍረስ አደጋ ለመታደግ የተለያዩ አካላትን በማስተባበር የ100 ሚሊየን ብር ድጋፍ መደረጉን አመልክተዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ የተጫዋቹ እና የማህበሩ ብቻ ሳይሆን አንዱ የከተማችን ጠንካራ ክለብ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያንና ከተማዋን የወከለ ታሪካዊ የስፖርት ክለብ ከመፍረስ የመታደግ ኃላፊነት እንዳለብን እናምናለን ሲሉም ነው የተናገሩት ከንቲባዋ በመልዕክታቸው።
ይህ አንጋፋ የስፖርት ክለብ ላለፋት 6 ወራት ደመወዝ መክፈል የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሶ እና የመበተን አደጋ ተጋርጦበት እንደነበር አውስተዋል።
በክለቡ ላይ የተጋረጠውን አደጋ ማየት ስለሌብን ከከተማው በጀትም ወስነን፣ ለባለሀብቶች ባቀረብነው ጥያቄ መሰረት ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እና ቢጂአይ ኢትዮጵያ በሰጡን ፈጣን ምላሽ በጥቅሉ የ100 ሚሊየን ብር ድጋፍ ለተቋቋመው ጊዜያዊ ኮሚቴ አስረክበናል ነው ያሉት።
ለከተማችን ወጣቶች፣ ለስፖርት ቢሮ እና ድጋፍ ላደረጉት ተቋማት በስፖርቱ ቤተሰብ ስም ምስጋናዬን ማቅረብ እወዳለሁ ሲሉም ገልጸዋል ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
ይህ ድጋፍ ከተማ አስተዳደሩ ክለቡን ከውድቀት ለመታደግና ለስፖርት ወዳድ ህዝብ የሰጠው ክብር አንዱ ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ሁሉንም ባሳተፈ እና በግልፅነት አዲስ ቦርድ መርጦ ከገጠመው ጊዜያዊ ችግር ተላቆ ወደ ቀድሞ ጥንካሬውና ዝናው የሚመለስበት ጊዜ ቅርብ እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል ከንቲባዋ በመልዕክታቸው።