የዲጂታል ፋይናንስ የማጭበርበር ወንጀሎችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመግታት ቅንጅታዊ አሰራሮች ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ፋይናንስ የማጭበርበር ወንጀሎችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመግታት ቅንጅታዊ አሰራሮች ይጠናከራሉ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንስ የማጭበርበር ወንጀሎችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመግታት የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የፍትህ ሚኒስትር ሃና አርአያስላሴ ገለጹ።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው እና የዲጂታል ፋይናንስ ማጭበርበርን መከላከል ላይ ትኩረት ያደረገ አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው።
"ደህንነቱ የተጠበቀ የፋይናንስ ስርዓት ለሀገር ዕድገት" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ባለው አውደ ጥናት ላይ የዲጂታል ፋይናንስ ማጭበርበር በኢትዮጵያ ያለበትን ደረጃ የሚያሳይ የዳሰሳ ጥናት ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት ይጠበቃል።
የፍትህ ሚኒስትር ሃና አርአያስላሴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ተግባራዊ በተደረገው የዲጂታል ፋይናንስ ስርዓት በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤቶች ተገኝተዋል።
ዲጂታል ስትራቴጂ 2025ን ጨምሮ በዲጂታል 2030 ለዲጂታል ፋይናንስ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸው ይህም ለዜጎች የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም የዲጂታል ፋይናንስ ደህንነትን ለማስጠበቅና ከማጭበርበር ወንጀሎች ለመከላከል በትኩረት መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ይህንንም ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራሮች እንደሚጠናከሩ አመልክተው፤ የፍትህ አካላት፣ የጸጥታና ደህንነት ተቋማትን ጨምሮ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ ነው ብለዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ በበኩላቸው፤ አውደ ጥናቱ የዲጂታል ፋይናንስ የማጭበርበር ወንጀለኞችን ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራትን ለማቀናጀት ያለመ መሆኑን አብራርተዋል።
በአውደ ጥናቱ የጥናት ውጤቶችን መሰረት ያደረጉ የመፍትሔ ሃሳቦች ቀርበው በባለድርሻ አካላት ውይይት እንደሚደረግባቸውም ተናግረዋል።
የህግ ክፍተቶችን መለየትና የቁጥጥር ስራዎችን ማጠናከር ሌላው የአውደ ጥናቱ ዓላማ መሆኑንም አስረድተዋል።