በአፋር ክልል የአዋሽ ወንዝን በመጠቀም በመስኖ የለማው የሣር መኖ እርሻ፣ የተፈጥሮን ልግስና በአግባቡ የመጠቀማችን ማሳያ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል የአዋሽ ወንዝን በመጠቀም በመስኖ የለማው የሣር መኖ እርሻ፣ የተፈጥሮን ልግስና በአግባቡ የመጠቀማችን ማሳያ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2018(ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል የአዋሽ ወንዝን በመጠቀም በመስኖ የለማው የሣር መኖ እርሻ፣ የተፈጥሮን ልግስና በአግባቡ የመጠቀማችን ማሳያ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት በአፋር ክልል ዞን አንድ፣ አይሳይታ ወረዳ፣ የአዋሽ ወንዝን በመጠቀም የለማውን የሣር እና መኖ እርሻን ጎብኝተናል ብለዋል።
በወረዳው 2 ሺህ 540 ሄክታር ላይ እየለማ የሚገኘውን የእንስሳት መኖ ሣር፣ የማምረት የማቀነባበር እና ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የማቅረብ ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በመስኖ ሥራው ለአካባቢው አርብቶ አደር የቴክኖሎጂ እና የተሻሻለ የዘር ሽግግር እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት በመልዕክታቸው።
በማሳው ላይ ለእንስሳት የወተት ምርታማነት ወሳኝ የሆኑ የሣር ዓይነቶች እየተመረቱ እንደሚገኙ አይተናል ብለዋል።
በመስኖ የሣር ልማት እና ማቀነባበር ለ1ሺህ ዜጎቻችን የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ሲሉም አክለዋል።
ከእንስሳት ሀብት ልማት ማሳደጊያነቱ በተጨማሪ ለሌማት ትሩፋት ሀገራዊ ኢንሼቲቭ ታላቅ አስተዋጽዖ እያበረከተ ነው ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት።
በአፋር የአዋሽ ወንዝን በመጠቀም የተሠራው የመስኖ ሥራ ለሌላውም የኢትዮጵያ አካባቢ ዝናብን ጠብቆ ከማምረት ይልቅ በየአቅጣጫው ያሉ ወንዞቻችንን መጠቀም እንደሚገባ የሚያስተምር ነው ብለዋል።