ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በቀሰሙት ዕውቀት ሀገራቸውንና ማህበረሰባቸውን ማገልገል ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በቀሰሙት ዕውቀት ሀገራቸውንና ማህበረሰባቸውን ማገልገል ይጠበቅባቸዋል
ጅግጅጋ፤ መጋቢት 19/2018(ኢዜአ)፦ ተመራቂ ተማሪዎች በቀሰሙት ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅመው ሀገራቸውንና ማህበረሰባቸውን ለማገልገል መዘጋጀት እንዳለባቸው የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ኡስማን አስገነዘቡ።
ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ በጤናና በሌሎች የትምህርት መስኮች አስተምሮ ዛሬ ለምረቃ ካበቃቸው 907 ተማሪዎች መካከል 237ቱ ሴቶች መሆናቸው ተገልጿል።
የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ኡስማን በምረቃ ስነ-ስርአቱ ላይ እንደተናገሩ፤ መንግስት ለትምህርት ዘርፉ ትኩረት በመስጠት በየመስኩ የሚያስፈልገውን የሰለጠ የሰው ኃይል በማፍራት ላይ ይገኛል።
ይህም ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት መውጣት የሚያስችል ወሳኝ አቅጣጫ እየተከተለ መሆኑን የሚያመላክት እንደሆነም ነው የተናገሩት።
ተመራቂ ተማሪዎች ሀገሪቱ የያዘችውን የብልጽግና ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ በእውቀትና በምርምር መስክ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።
በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ለሀገር እና ለህዝብ ለሚጠቅሙ ተግባራት ትኩረት በመስጠት ሊሰሩ እንደሚገባም እንዲሁ።
የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሰኢድ መሀመድ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ብቁ እና የተማረ የሰው ሀይል ለማፍራት ባከናወናቸው ተግባራት እስከ 50ሺህ የሚጠጉ ዜጎችን አስተምሮ ማስመረቅ ችሏል ብለዋል።
የዛሬ ተመራቂዎችም በቆይታቸው ያገኙት ዕውቀት የመደመር እሴት ድልድይ በመሆን ለሀገር ብልጽግና መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
ተመራቂዎች የዛሬ ስኬታቸው ለነገ የተሻለ እውቀት የሚዘጋጁበትና ትልቅ ማህበራዊ ኃላፊነት የሚሸከሙበት መሆኑን ተረድተው ሊሰሩ እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።