ቀጥታ፡

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የመፍጠር እና የመፍጠን ዕሳቤን በተጨባጭ ያሳየ ተቋም ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2018(ኢዜአ)፦ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የመፍጠር እና የመፍጠን ዕሳቤን በተጨባጭ ያሳየ ተቋም ነው ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር እና የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዓለምፀሐይ ጳውሎስ ገለጹ።

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ምስረታ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል "በአዲስ ምዕራፍ ለተሻለ ነገ" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ መርሀ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል።

በመርሀ ግብሩ ኮርፖሬሽኑ በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ ሕንጻዎችን አስመርቋል።


 

በዚህም ኮርፖሬሽኑ በፒያሳ ለወርቅ ንግድ ሱቆች አገልግሎት እንዲውል ተደርጎ የተገነባውን ዘመናዊ የንግድ ሕንፃ (ጎልድ ሞል) እና በአዲስ አበባ በተለምዶ ሱማሌ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ያስገነባው ለመኖሪያ እና ለንግድ ቅይጥ ጥቅም የሚውለውን ባለ 27 ወለል ሕንፃ አስመረቋል።

በተጨማሪም ሀገራዊ ለውጡን መነሻ አድርጎ ኮርፖሬሽኑ በተቋማዊ ሪፎርሙ ያስመዘገበውን ስኬት የሚያስቃኝ ኤግዚቢሽን ተከፍቷል።

ከኮርፖሬሽኑ ጋር አብሮ ለመሥራት ስምምነት ላይ የደረሱ የአውሮፓ የግንባታ ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በኤግዚቢሽኑ እየተሳተፉ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር እና የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዓለምፀሐይ ጳውሎስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኮርፖሬሽኑ በቤት ልማት አስተዳደር ዘርፍ ግንባር ቀደም ተቋም ነው።

ከለውጡ በፊት ተቋሙ በቤት ልማት እና አቅርቦት መካከል ያለውን ሰፊ ክፍተት ከመሙላት ይልቅ ያሉትን ቤቶች በማስተዳደር ላይ ተወስኖ እንደቆየ አስታውሰዋል።

ኮርፖሬሽኑ ከዚህ ችግር ለመውጣት ሀገራዊ ለውጡን መነሻ በማድረግ ተቋማዊ ሪፎርም ማከናወኑን ጠቁመው ይህም ኮርፖሬሽኑ ከነበረበት ውስብስብ ችግር በመውጣት በአጭር ጊዜ ለስኬት እንደበቃ ገልጸዋል።

በጉባ የተበሰረውን የአንድ ነጥብ አምስት ሚልየን ቤቶች ግንባታ ሀገራዊ ፕሮጀክትን ለማሳካት ትልቁን ድርሻ ከሚይዙ ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የመፍጠር እና የመፍጠን ዕሳቤን በተጨባጭ ያሳየ ተቋም መሆኑን ገልጸው፤ ኮርፖሬሽኑ ያስመዘገባቸውን ስኬቶች ማስቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት አስደማሚ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

በውስብስብ ችግር ውስጥ የነበረው ተቋም ከችግሩ ተላቆና ከመክሰም ተርፎ ስኬታማና የተጣለበትን ሀገራዊ ሀላፊነት መወጣት የሚችል ሞዴል ተቋም መሆኑን ጠቁመዋል።

በኋላ ቀር አስተሳሰብ ተተብትቦ የቆየውን አተገባበር በማስቀረት ዘመናዊ አሰራር መዘርጋት መቻሉንና ይህም ተቋሙ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ እንዲሆን ማስቻሉን ተናግረዋል።

ኮርፖሬሽኑ ዛሬ ያስመረቀው ዘመናዊ የንግድ ሕንጻ(ጎልድ ሞል) እና ባለ 27 ወለል ሕንጻ ለኮርፖሬሽኑ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ጠቁመዋል።

በቀጣይም በቀጣናው ተወዳዳሪ የኮንስትራክሽን ተቋም ለመሆን ስራውን በላቀ መንገድ እንደሚያከናውን አረጋግጠው ለኮርፖሬሽኑ ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

በመርሀ ግብሩ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር እና የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዓለምፀሐይ ጳውሎስ፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ መለስ መና፣ የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፣ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል(ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም