ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማት ስኬት የፖሊሲና የአመራር ቁርጠኝነት ተጨባጭ ውጤቶች ናቸው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማት ስኬት የፖሊሲና የአመራር ቁርጠኝነት ተጨባጭ ውጤቶች መሆናቸውን የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴዔታ በርኦ ሀሰን ገለጹ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአዲስ አበባ የገነባውን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ኃይል መሙያ ጣቢያ (ኢቪ-ቻርጅ) አስመርቋል።

በምርቃት ሥነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴዔታ በርኦ ሀሰን፤ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል አቅርቦት ለአየር ንብረት ተፅዕኖ የማይበገር ከፍተኛ አቅም አላት ብለዋል።

ይህም የኢትዮጵያን የነዳጅ ጥገኝነትና የውጭ ምንዛሬ ወጪን በማስቀረት የኃይል አቅርቦት ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።


 

በዚህም የትራንስፖርት ዘርፉን በታዳሽ የኃይል አማራጭ ለመተካት በሚደረገው ጥረት አሁን ላይ 140 ሺህ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኃይል አቅርቦት ፋላጎትን ለማሟላትም በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በርካታ የተሽከርካሪ ኃይል መሙያ ጣቢያዎችን በመገንባት እንዲሰሩ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኃይል መሙያ ጣቢያዎች ግንባታም የነዳጅ ጥገኝነትን በማስቀረት የኃይል ሉዓላዊነት የሚያጎናፅፍ እንደሆነ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ልማት ያስገኘችው ስኬትም የፖሊሲና የአመራር ቁርጠኝነት ተጨባጭ ውጤቶች ማሳያ እንደሆነ አብራርተዋል።


 

የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ጌቱ ገረመው በበኩላቸው፤ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መሙያ ጣቢያ ግንባታ ከኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር የተጣጣመ ነው ብለዋል።

ለዚህም የኃይል አቅርቦት አስተማማኝነትን በማረጋገጥ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኃይል መሙያ ጣቢያ ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በቀጣይም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሽከርካሪ ኃይል መሙያ ጣቢያዎችን በስፋት የመገንባት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም