ቀጥታ፡

ተመራቂዎች ለማህበረሰብ አገልግሎት ቅድሚያ በመስጠት ችግር ፈቺ ተግባራትን ማከናወን ይገባቸዋል

ወላይታ ሶዶ፤ መጋቢት 19/2018(ኢዜአ)፦ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች ለማህበረሰብ አገልግሎት ቅድሚያ በመስጠት ችግር ፈቺ ተግባራት ላይ ማተኮር እንደሚገባቸው ተጠቆመ።

ዩኒቨርሲቲው በዛሬው ዕለት በ19ኛው ዙሩ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 2ሺህ 307 ተማሪዎች ያስመረቀ ሲሆን፤ ከተመራቂዎቹ መካከል 587ቱ ሴቶች መሆናቸው ተመላክቷል።


 

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ አባል እና የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ከዲጃ ሁሴን(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራው ጎን ለጎን የተለያዩ የማህበረሰብ አገልግሎቶችን በማከናወን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

ተመራቂዎች ከዩኒቨርሲቲው በቀሰሙት ዕውቀት ለማህበረሰብ አገልግሎቶች ቅድሚያ በመስጠት ችግር ፈቺ ተግበባራትን ማከናወን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

አክለውም ተመራቂዎች የቀሰሙትን ዕውቀትና ክህሎት በተግባር ላይ በማዋል የተጀመረውን ሁለንተናዊ ለውጥና ዕድገት ለማስቀጠል ህዝባቸውን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጉቼ ጉሌ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው በበጀት ዓመቱ ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት ብቁ ዜጎችን ለማፍራት ባደረገው ርብርብ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።


 

የትምህርት ጥራት ደረጃን ለማሻሻልና የመምህራንን አቅም ለማሳደግም የውጭና የሀገር ውስጥ የትምህርት ዕድሎችን በማመቻቸት ደረጃቸውን እንዲያሳድጉ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህም ከመማር ማስተማር ባሻገር የማህበረሰብ አገልግሎት፣ የምርምር ስራዎች እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎች ጎልተው እንዲወጡ ማድረጉን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ሀገሪቱ የምትፈልገውን ጥራት ያለው የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት እንዲሁም የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶችን በስፋት የማከናወን ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም