ቀጥታ፡

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለዳበረ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ አዲስ ምዕራፍ የምንከፍትበት ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2018(ኢዜአ)፦ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ፉክክር በማድረግ ለዳበረ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ አዲስ ምዕራፍ የምንከፍትበት መድረክ ነው ሲሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24/2018 ዓ.ም ድምፅ በሚሰጥበት የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 28/2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ ይገኛል።

የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አማራጭ ሃሳቦችን ለህዝብ በማቅረብ ድምፅ ማግኘት የሚያስችላቸውን ዝግጅት እያደረጉ ነው።

በሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫም ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ፉክክር በማድረግ ለኢትዮጵያ የዳበረ የመድበለ ፓርቲ ባህል ግንባታ እንደሚጠቀሙበት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) ዋና ጸኃፊ ዋሲሁን ተስፋዬ፤ የኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ለዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ወሳኝ የልምምድ ዕድል እንዳለው ተናግረዋል።

ይህም ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ፉክክር በማድረግ የዳበረ የመድበለ ፓርቲ ምኅዳር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ገንቢ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን አንስተዋል።

ለአብነትም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) በራሱ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ጠቅላላ ጉባኤውን በማካሄድ ዴሞክራሲያዊ የአመራር ለውጥ ማድረጉን አስረድተዋል።

የፖርቲው ውስጠ-ዴሞክራሲም የሀገርን የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ለማጠናከር ጉልህ ድርሻ እንዳለው አንስተዋል።


 

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሕብረት(ኢዴሕ) ሊቀመንበር ገብሩ በርሔ፤ መንግስት ሰፊ የፖለቲካ ምኅዳር እንዲፈጠር በማድረግ አስደናቂ ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትም የፓርቲዎችን ሚዛናዊነት ማስጠበቅ የሚያስችል ምቹ የድጋፍና ክትትል ሥርዓት መፍጠሩን ገልጸዋል።

ፓርቲያቸውም የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ፉክክር ባህል በማጎልበት ለመድበለ ፓርቲ ግንባታ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ አንተዋል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሐዊና ገለልተኛ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስቻይ ሁኔታ ፈጥሮ እየሰራ ነው ያሉት ደግሞ የአገው ብሄራዊ ሸንጎ ምክትል ፕሬዝዳንት ፍትሕዓለው ዓባይ ናቸው።


 

በዚህም ሰላም ለኢትዮጵያ የፓርቲዎች ጥምረት በሕዝብ ተወካዮችና በክልል ምክር ቤቶች የሚወከሉ ዕጩዎችን በማቅረብ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ የፉክክር ሂደትም አማራጭ የፖሊሲ ሀሳባቸውን በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ለህዝብ በማቅረብ ለዴሞክራሲ ባህል ግንባታ እየተጠቀሙበት እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በህዝብ ይሁንታ የተመሰረተ መንግስት በማቋቋም ጠንካራ የዴሞክራሲ ባህል ለመገንባት ዜጎች በምርጫ ሂደት የሚሰጡት ድምፅ ከፍተኛ ዋጋ እንዳለውም ጠቁመዋል።

ለዚህም የፓርቲዎቻቸውን አመራር፣ አባላትና ደጋፊዎች የምርጫን ዋጋ በማስገንዘብ የዴሞክራሲ ባህልን ለማጎልበት በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆኑን አረጋግጠዋል።

መራጩ ህዝብም የምርጫ ካርድ በማውጣት ይበጀኛል ለሚለው ፓርቲ ድምፅ መስጠት የሚያስችል ዝግጅት ማድረግ እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም