የኮደርስ ስልጠና ዲጂታል የፈጠራ ስራዎችን ለማሳደግ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኮደርስ ስልጠና ዲጂታል የፈጠራ ስራዎችን ለማሳደግ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ዲጂታል የስራ ፈጠራ እድሎችን እና የፈጠራ ስራዎችን በማስፋት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን እያሳደገ መሆኑን የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተጀመረው የአምስት ሚሊየን የኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠና በተለይም ወጣቶች የእድሉ ተጠቃሚ ሆነው ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን የሚያሳድግ መሆኑ ይታወቃል።
በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ዜጎች ስልጠናውን እየወሰዱ ከራሳቸው አልፈው ለሀገራቸው የዲጂታል ልማት ስትራቴጂ ትግበራ አሻራቸውን እያኖሩ ይገኛሉ።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ስልጠናው የዜጎችን ዲጂታል ክህሎት በማሳደግ የአኗኗር ዘይቤን የሚያሳልጡ ክህሎቶችን ለማጎልበት ያስችላል።
በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶች ያላቸውን ክህሎት በማሳደግ ወደ ፈጠራ ስራዎች እንዲሸጋገሩ እገዛ አድርጓል ብለዋል።
ይህም የሀገሪቱን ተወዳዳሪነት በማሳደግ ወደ እውቀት መር ኢኮኖሚ ለሚደረገው ሽግግር አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
በትምህርት፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝምና ሌሎች ዘርፎች በዲጂታል ስርዓት እንዲታገዙ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።
በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የአይ ሲቲ ዳይሬክተር ናኦል አንበሴ በበኩላቸው፤ በኢንስቲትዩቱ ተማሪዎችና ሰራተኞች ስልጠናውን እንዲወስዱ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ተጨማሪ ክህሎትን ለማጎልበት የሚረዳ በመሆኑ ዜጎች እድሉን በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል ብለዋል።
የአይሲ ቲ ባለሙያዋ ጥሩ መልካም ስልጠናው በየትኛውም ሙያ የተሰማሩ ዜጎች ስራቸውን ለማሻሻል ያለውን ሚና ገልጻለች።
ተማሪ ባዩሽ ተስፋዬ እና ከደቡብ ሱዳን የትምህርት ስኮላርሺፕ ተጠቃሚ የሆነው ላዱሊ ሞሪ ስልጠናው ከዲጂታል ዘመን ጋር አብሮ ለመራመድ ክህሎትን ለማሳደግ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።