ቀጥታ፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚመደብላቸውን ነፃ የአየር ሰዓት በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2018 (ኢዜአ)፦ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚመደብላቸውን ነፃ የአየር ሰዓት በመጠቀም ፕሮግራሞቻቸውን በአግባቡ ማስተዋወቅ እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስገነዘበ።

የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነፃ የአየር ሰዓት ድልድል የዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሀይሉ በዚሁ ወቅት፤ ቦርዱ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከሚያደርጋቸው ዝግጅቶች መካከል አንዱ ለፓርቲዎች ነፃ የአየር ሰዓት ድልድል ማድረግ ነው ብለዋል።


 

ይህ የነፃ የአየር ሰዓት ድልድል የሚካሄደውም ቦርዱ ከመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ጋር በመሆን ባበለጸገው አዲስ ሲስተም መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህ አሰራር የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን ሀሳብ፣ ፖሊሲ እና ፕሮግራም ለመራጩ ህዝብ እንዲያስተዋውቁ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰው፤ ፓርቲዎች የሚመደብላቸውን ነፃ የአየር ሰዓት በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በተለይም ፓርቲዎቹ ባስመዘገቧቸው ሴት እና አካል ጉዳተኛ ዕጩዎች ብዛት ልክ ተጨማሪ ነፃ የአየር ሰዓት የሚፈቅድ አዋጅ በመፅደቁ፤ አሰራሩ በዚህ ምርጫ ተግባራዊ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀይማኖት ዘለቀ በበኩላቸው፤ ነፃ የአየር ሰዓቱ መራጩ ህዝብ ድምፅ በሚሰጥበት ወቅት በዕውቀት ላይ ተመስርቶ እንዲወስን ያስችላል ብለዋል።


 

ነፃ የአየር ሰዓቱ ለ47 የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ለግል ዕጩ ተወዳዳሪዎች በዕጣ ድልድል እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የዘንድሮው ድልድል ከ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ጋር ሲነጻጸር የ10 በመቶ ብልጫ እንዳለው ጠቁመው፤ ይህም በ50 መገናኛ ብዙሃን (በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን እና በጋዜጣ) የሚስተናገድ ይሆናልም ብለዋል።

ይህ ድልድል ምርጫው ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ትልቅ አስተዋፅኦ ስላለው፣ ፓርቲዎች የአየር ሰዓቱን በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እንዲጠቀሙ አስገንዝበዋል።

መገናኛ ብዙሃንም ለፓርቲዎቹ አስፈላጊውን የቴክኒክ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።

የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነፃ የአየር ሰዓት አጠቃቀም ቅዳሜ፣ እሁድ እና የበዓላት ቀናትን ሳይጨምር ከመጋቢት 23 እስከ ግንቦት19 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ተፈፃሚ እንደሚሆን ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም