ቀጥታ፡

በምርጫው በንቃት በመሳተፍ የሚወክለንን ለመምረጥ ካርድ እየወሰድን ነው

ቡታጅራ ፤መጋቢት 19/2018 (ኢዜአ)፦ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት በመሳተፍ የሚወክለንን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ እየወሰድን ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቡታጅራ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።   

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት፣ በመጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄድ ሲሆን፤ ለዚሁ ተግባር የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅቶች በመከናወን ላይ ይገኛሉ።   

ከእነዚህ ዝግጅቶች መካከል ዜጎች የመምረጥ መብታቸውን ለመጠቀም የሚያስችላቸውን የመራጭነት ካርድ እየወሰዱ ይገኛሉ።   

ኢዜአ በቡታጅራ ከተማ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ በቀጣዩ ምርጫ ለመሳተፍና የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት የምርጫ ካርድ እየወሰዱ ይገኛሉ።   

በከተማዋ የእርንዛፍ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ባህርነሽ መሀመድ፤ "የመራጭነት ካርድ በመውሰድ የሚጠቅመኝን ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ" ብለዋል።   

የምርጫ ካርድ መያዝ ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም እንዲችሉ ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ፣ ሁሉም የምርጫ ካርድ መያዝ እንዳለበትም ይመክራሉ።  

ሌላኛው የከተማዋ የ02 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ቢራቱ ጠረጋ በበኩላቸው፤ የሕዝብን የልማት ፍላጎትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ፓርቲ ለመለየት የምርጫ ክርክሮችን በንቃት እየተከታተሉ መሆኑን ጠቁመዋል።   


 

የአካል ጉዳተኛ የሆኑት አቶ ቢራቱ፤ በምርጫው አካል ጉዳተኞችን በትምህርትና በሥራ እድል ተሳታፊ እና ተጠቃሚ የሚያደርግ ፓርቲ እንደሚመርጡ ተናግረዋል።   


 

በከተማዋ የ04 ሸባብ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ከድጃ ሳሉሲን እና የ03 ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሪት መለሰች ተካም እንዲሁ፤ የሕዝቡን የልማት ጥያቄ የሚመልስ ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።


 

የካርድ አሰጣጥ ሂደቱም ምቹ እና ቀልጣፋ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመስቃንና ማረቆ ምርጫ ክልል 1 አስፈጻሚ አቶ እስጢፋኖስ ፍቃዱ፤ ከየካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ መራጮች እየተመዘገቡ መሆኑን አረጋግጠዋል።   

በምርጫ ክልሉ በሚገኙ 87 የምርጫ ጣቢያዎች በሙሉ በቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የመራጮች ምዝገባ ሂደት በተሳካ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም