በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዘንድሮው የበልግ እርሻ ከ670 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዘንድሮው የበልግ እርሻ ከ670 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል
ዲላ፤ መጋቢት 19/2018 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዘንድሮው የበልግ እርሻ ከ670 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
በሁሉም የበልግ አብቃይ አካባቢዎች እየጣለ ያለውን ዝናብ በአግባቡ በመጠቀም የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው።
በዚህም መሰረት በሁሉም አካባቢዎች የግብርና ልማት ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አድማሱ አወቀ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በክልሉ ከበልግ እርሻ ዝግጅትና የዘር እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ውጤታማ የሆኑ ስራዎች እየተካሔዱ ነው።
በዘንድሮው የበልግ ወቅትም ለማልማት ከታቀደው 987 ሺህ 314 ሄክታር መሬት 670 ሺህ 530 ሄክታሩ በዘር መሸፈኑን ነው የተናገሩት።
ከበልግ እርሻው በተጓዳኝም በ 82 ሺህ 202 ሄክታር መሬት ላይ የእንስሳት ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ስራዎች በስፋት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
ለዚሁ የእርሻ ስራ ቀደም ብሎ የግብአት አቅርቦት ዝግጅት መደረጉን አመልክተው ስራው በተሳካ ሁኔታ እየተካሔደ መሆኑን አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት በየደረጃው ያሉ አመራሮች፣ የግብርና ባለሙያዎችና የአርሶ አደሮች ጠንካራ ትብብር በማድረጋቸው ውጤታማ እንቅስቃሴ እንዲኖር እያደረገ ነው ብለዋል።
በዘርፉ የተቀመጠውን እቅድ ሙሉ ለሙሉ ለማሳካትም በየደረጃው ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።