በባህር ዳር ከተማ በሶስተኛው ምአራፍ እየተካሔደ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ እየተፋጠነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በባህር ዳር ከተማ በሶስተኛው ምአራፍ እየተካሔደ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ እየተፋጠነ ነው
ባህር ዳር፣መጋቢት 19 /2018(ኢዜአ)፡- በባህር ዳር ከተማ በ3ኛው ምእራፍ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ እየተፋጠነ እንደሚገኝ ከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።
የኮሪደር ልማት ስራ ግንባታ ብቻ ሳይሆን ከተሞችን ወደ ላቀ ምቹ፣ ንቁ እና ዘላቂ የመኖሪያ ከባቢ የመለወጥ ጥረቶች የታየበት መሆኑ ይታወቃል።
የልማት ስራው በተለይ ሥነ-ውበትን በማሳደግ፣ አረንጓዴነትን በማስፋት ብሎም መሰረተ ልማትን በማሻሻል የህዝቦችን ጤና መጠበቅ ብቻ ሳይሆን የስራ ዕድሎችንም እየፈጠረ ይገኛል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተሻገር አዳሙ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኮሪደር ልማት ስራ መጀመሩ ከተማዋን በማሳደግ ለቱሪዝም፣ ለኢንቨስትመንትና ለኑሮ ምቹ እንድትሆን አድርጓታል።
በዚህም ለከተማዋ እድገት እያስገኘ ያለውን ጥቅም ለማስፋት ከግዮን አደባባይ እስከ ዘጌ መገንጠያና አባይ ማዶ የስምንት ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ግንባታ እየተፋጠነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት ብቻ እየተካሄደ በሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራም ለ21 ሺህ ወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠሩም ባሻገር በቀንና በምሽት በመስራት የወጣቱንና የባለሙያውን የስራ ባህል ለመቀየር እንዳስቻለ ነው የሚገልጹት።
ከዚህ በፊት በሁለት ምእራፍ የተገነቡት ስምንት ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር የአስፋልት፣ የእግረኛና የሳይክል መንገዶችን፣ የማረፊያና የአረንጓዴ ቦታዎች፣ ፋውንቴኖችንና ሌሎች መዝናኛዎች ለአገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው ብለዋል።
ይህም ከተማዋን ጽዱ፣ ውብ፣ ማራኪና ነፋሻማ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ነው የገለጹት።
ማህበረሰቡ ባለፈው ዓመት ለተካሔደው የኮሪደር ልማት ስራ ከ500 ሚሊየን ብር በላይ ማዋጣቱን ጠቁመው ዘንድሮም በገንዘብ ፣ በጉልበትና በእውቀት የሚያደረገው ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዋል።
የኮሪደር ልማቱ አዲስ የሥራ እድል በመፍጠር እውቀትና ልምድ እንድናገኝ አድርጎናል ያለው ደግሞ በባዞላ ማንጠፍ የስራ እድል ተጠቃሚ የሆነው ወጣት ሀብታሙ አረጋ ነው።
የኮሪደር ልማቱ የሚባክን ጊዜን በማስቀረት ምሽት ጭምር ከመስራት ባሻገር የስራ ባህልን በመቀየር አልባሌ ቦታ ከመዋል አድኖኛል ነው ያለው።
በኮሪደር ልማቱ በጠቅላላ ተቆጣጣሪነት የተሰማሩት አቶ እሸቱ እሚያምረው በበኩላቸው፤የኮርደር ልማት ስራው እሳቸውን ጭምሮ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንዳስቻላቸው አመልክተዋል።
በቀጣይም ባገኙት ልምድና እውቀት በመጠቀም የተሻለ ስራ ለመስራት መነሳሳት እንደፈጠረላቸው ነው የገለጹት።