በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በመጪው ክረምት የሚተከሉ ችግኞች ዝግጅት በስፋት እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በመጪው ክረምት የሚተከሉ ችግኞች ዝግጅት በስፋት እየተከናወነ ነው
አምቦ፤ መጋቢት 19/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በመጪው ክረምት የሚተከሉ ችግኞች ዝግጅት በስፋት እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።
በጽህፈት ቤት የደን ልማት ባለሙያ ጉደታ ጡሪ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ እየተዘጋጁ ከሚገኙ ችግኞች መካከል ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ዝርያዎች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
በክረምቱ ወራት አጠቃላይ ከ94 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የችግኝ ተከላ እንደሚከናወን ገልጸው፤ የችግኝ ማፍላት ስራው በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ባሳተፈ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ዝግጅቱ የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዲቻል ምርታማነታቸው ከፍተኛ በሆኑና በተሻሻሉ የችግኝ ዝርያዎች ላይ ትኩረት ማድረጉንም ጠቅሰዋል።
ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሮች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተው፤ ችግኞችን የመንከባከብና የመጠበቅ ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑንም አክለዋል።
የተተከሉ ችግኞች የአካባቢ ስነ-ምህዳርን ከመቀየር አንጻር ከፍተኛ ሚና ከመጫወታቸው ባለፈ፣ ደርቀው የነበሩ ኩሬዎች ዳግም ውሃ እንዲይዙ በማድረግ ለአርሶ አደሩ ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል ነው ያሉት።
ባለፉት ሰባት ዓመታት በድምሩ 616 ሺህ 613 ሄክታር መሬት ላይ ችግኞች መተከላቸውን አስታውሰው፤ የአካባቢው ማህበረሰብ ያለውን ደን የመጠበቅ ባህላዊ እሴት ለአረንጓዴ ልማት ስራው ስኬታማነት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል።