“ኢንቨስት ኢን ኢትዮጵያ 2026” ፎረም በ13 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር የኢንቨስትመንት ውሎች ፊርማ ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
“ኢንቨስት ኢን ኢትዮጵያ 2026” ፎረም በ13 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር የኢንቨስትመንት ውሎች ፊርማ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2018(ኢዜአ)፦ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው አራተኛው “ኢንቨስት ኢን ኢትዮጵያ 2026” ፎረም ዛሬ ተጠናቋል።
በፎረሙ ላይ የተለያዩ ዋና ዋና ዘርፎችን ያካተቱና በአጠቃላይ 13 ነጥብ 1 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር የሚገመቱ የኢንቨስትመንት ውሎች ተፈርመዋል።
በፎረሙ መጨረሻ የተከናወነው የፊርማ መርሃግብር በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና እና አግሮ-ፕሮሰሲንግ፣ በኃይል፣ በማዕድንና በሌሎች ዘርፎች ትልልቅ የኢንቨስትመንት ስምምነቶችን ያካተተ ነው።
የተፈረሙት ውሎች በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ያለውን የኢንቨስተሮች እምነት እንደሚያሳይ ተገልጿል።
በተጨማሪም ለስራ ፈጠራ፣ ለውጭ ምንዛሬ ግኝትና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ተጠቅሷል።
በተመሳሳይ በ“ኢንቨስት ኢን ኢትዮጵያ 2025” ፎረም በአጠቃላይ 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር የሚገመቱ የኢንቨስትመንት ውሎች መፈረማቸው የሚታወስ ሲሆን እነዚህም ፕሮጀክቶች አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ መግባታቸው ይታወቃል።
ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ እንደ ግንባር ቀደም የኢንቨስትመንት መዳረሻ እየታየች መሆኗን ያመላክታል።
ፎረሙ አዳዲስ አጋርነቶችን ለመፍጠርና ቀጣይ የኢንቨስትመንት ግንኙነቶችን ለማጎልበት ጠንካራ መድረክ መሆኑን መረጋገጡን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።