የአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓሲፊክ ሀገራት ድርጅት የአባል ሃገራቱን ጥቅም ለማስከበር መትጋት ይጠበቅበታል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓሲፊክ ሀገራት ድርጅት የአባል ሃገራቱን ጥቅም ለማስከበር መትጋት ይጠበቅበታል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2018 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓሲፊክ ሀገራት ድርጅት የተቋቋመለትን አላማ እንዲያሳካ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ነጻነቱን ጠብቆ መጓዝ እንደሚገባው በቤልጂየም፣ ኔዘርላንድስ እና ሉክስምበርግ (ቤኔሉክስ) አገራት እና በአውሮፓ ህብረት ተቋማት የኢትዮጵያ አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን ገለጹ።
11ኛው የአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓሲፊክ ሀገራት ድርጅት (ኦ ኤስ ፒ ኤስ ) የመሪዎች ጉባኤ ነገ ይጀምራል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴን ጨምሮ በርካታ የሀገራት መሪዎች በጉባኤው ላይ ይሳተፋሉ።
የድርጅቱ የመሪዎች ጉባኤ ቅድመ ስብስባ ዛሬ ተካሄዷል።
በስብሰባው ላይ በቤልጂየም፣ ኔዘርላንድስ እና ሉክስምበርግ (ቤኔሉክስ) አገራት እና በአውሮፓ ህብረት ተቋማት የኢትዮጵያ አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን ተገኝተዋል።
አምባሳደር እሸቴ በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር የአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓሲፊክ ሀገራት ድርጅት ለአባል ሀገራቱም ሆነ ለመላው ዓለም ወሳኝ አስተዋጾኦ ማድረግ እንዲችል ራሱን በገንዘብ እና በመዋቅር ማጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል።
አስቸጋሪ በሆነው የዓለም ተቀያያሪ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ድርጅቱ የአባል ሀገራቱ ጥቅም እንዲከበር በትጋት መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።
አምባሳደር እሸቴ በተለይ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ድርጅቱ እ.አ.አ በ1975 ከቅኝ ግዛት በኋላ የተመሰረተ እና በቅኝ ግዛት ሲጎዱ ለነበሩ የአፍሪካ፣ ካሪቢያን እና ፓስፊክ ሀገራት አለኝታ እንዲሆን ታስቦ የተመሰረተ መሆኑን አስታውሰው ኢትዮጵያ ለዚህ ድርጅት መጠናከር ትኩረት ሰጥታ እንደምትንቀሳቀስ አስረድተዋል።
ባለፉት ጊዜያት የድርጅቱ በጀት በአውሮፓ ህብረት ድጋፍ ይሸፈን እንደነበረ ገልጸው ድርጅቱ የተቋቋመለትን አላማ እንዲያሳካ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ነጻነቱን ጠብቆ መጓዝ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ለዚህ ደግሞ አባል ሀገራቱ የሚጠበቅባቸውን የገንዘብ መዋጮ መክፍል እንደሚገባቸው ነው ያሳሰቡት።
በቅድመ ጉባኤ ስብሰባው የበርካታ ሀገራት ተወካዮች ድርጅቱ እያበረከተ ያለውን የማይተካ አስተዋጾኦ በማድነቅ የተሻለ ጠንካራ ሆኖ በሚወጣበት ጉዳይ ላይም ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
በአባል ሀገሪቱ ያለውን የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማሳደግ፣ የወጣቶችን አቅም በሚገባ መጠቀም ከዳያስፖራው ማህበረሰብ ጋር ያለን ትስስር በማሳደግ ለሁለንተናዊ እድገት መጠቀም የሚሉት በስፋት የተንሸራሸሩ ሀሳቦች ናቸው።
በአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓሲፊክ ሀገራት ያለውን ድህነት በማጥፋት ኢኮኖሚያዊ እድገትን ማፋጠንን አላማ በማድረግ የተመሰረተው ድርጅቱ በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት አይነተኛ የትብብር ማዕከል ሆኖ እያገለገለ ነው።
ከአውሮፓ ሀገራት ጋር ያለው የንግድ፣ ልማት፣ ዴሞክራሲ፣ አስተዳደር እና ሰብዓዊ ጉዳዮች ትብብር ደግሞ የደቡብ- ሰሜን ትስስርን በማጠናከር ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።