ቀጥታ፡

ወጣቶች የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ ፋንታ እንዲወስኑ በትምህርት ዝግጁ ማድረግ ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ወጣቶች የዓለምን ተለዋዋጭና ኢ-ተገማች ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት የሀገሪቷን የወደፊት ዕጣ ፋንታ እንዲወስኑ በትምህርት ዝግጁ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቆይታ ዓለም አቀፍ ተቋማት የደረሰባቸውን አደጋ፣ የርዕዮተ ዓለምና የሀያላት አሰላለፍ ለውጥ፣ የቴክኖሎጂ ልህቀት በአፍሪካ ላይ የሚያመጣውን ተጽዕኖና ቅድመ ዝግጅት በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በቆይታቸው የዓለም ተለዋዋጭና ኢ-ተገማች ነባራዊ ሁኔታ ለታዳጊ ሀገራት ፈታኝ መሆኑን በማንሳት፤ አስቸኳይና ወሳኝ ርምጃ ይፈልጋል ብለዋል፡፡

የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካውያን የህልውና ጥያቄ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ችግሩን ለመቋቋም ስልታዊ እሳቤና ዝግጅት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ፈተናዎችን ተጋፍጦ ለድል የሚበቃ ትውልድ ለመፍጠር ለሁኔታዎች የማይበገር የትምህርት ስርዓት መገንባት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ብሎም አፍሪካውያን ማድረግ የምንችለው ትልቁ ነገር የቀጣዩን ትውልድ በትምህርት በሚገባ ማዘጋጀት ነው ብለዋል፡፡

አፍሪካ በትምህርት ራሷን ለማዘጋጀት የቀጣዩን 50 ዓመት ልትጠቀምበት ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በትምህርት ስርዓቱ ላይ መሰረታዊ ለውጥ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የዓለምን ተለዋዋጭና ኢ-ተገማች ነባራዊ ሁኔታ ተቋቁሞ የኢትዮጵያን መፃኢ ዕድል ለመወሰን የተሟላ እውቀት፣ ብቁና ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን መላመድ የሚችል ትውልድ መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፉ ሪፎርም በማድረግ በሀገር አቀፍ ደረጃ የቅድመ መደበኛ ትምህርትን በማስፋፋት፣ የትምህርት መሰረተ ልማት በመገንባት፣ የሥርዓት ትምህርት ማሻሻያና ጥራት ማረጋገጫ ስራዎችን እያከናወነች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይሄውም ቀጣዩን ትውልድ የማብቃት አካል መሆኑን ገልጸው፤ በራሱ የሚተማመን ሀገርን የሚጠብቅና አፍሪካ ወደፊት ሊደርስባት ከሚችል አደጋ የሚከላከል ዜጋ መፍጠር ያስችላል ብለዋል፡፡

ትምህርት የትውልድ የህልውና ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት የሰጡት ሚኒስትሩ፤ ችግሩን ቀለል አድርጎ ማየት እንደማይገባ ገልጸዋል፡፡

ትምህርት ወጣቶች የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ አመዛዝነው እንዲረዱና የሌሎችን ከመኮረጅ ይልቅ በሀገር በቀል እሳቤ አዳዲስ ሀሳቦችን እንዲያመነጩ እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል፡፡

ለዚህም በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ በፖለቲካ፣ በፍልስፍናና በሌሎችም ዘርፎች ዓለም የሚያደርሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ ተቋቁመው ማሻገር የሚችሉ ብቃት ያላቸው አመራሮችን ማፍራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ትምህርት ከአካዳሚክ እውቀት ባለፈ እሴቶችንና ማህበራዊ ንቃተ ህሊናን ማካተት እንዳለበት ገልጸው፤ ትምህርት ቀጣዩን ትውልድ ለማዘጋጀትና ለማስተማር ትምህርት የህልውና ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የፖሊሲ አውጭዎች በወጣቶች ትምህርት ላይ መሰማራት የማህበራዊ ግብ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንስ በተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ ስትራቴጂያዊ ጉዳይ መሆኑን መረዳት አለባቸው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም