ቀጥታ፡

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያዘጋጀው የክርክር መድረክ መራጩ ህዝብ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ድምፅ እንዲሰጥ ምቹ መደላድል ይፈጥራል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያዘጋጀው ወጥ የሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክር መድረክ መራጩ ህዝብ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ድምፅ እንዲሰጥ ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሚወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ባዘጋጀው የመጀመሪያው የክርክር መድረክ ሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት(ሰላም)፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) ፓርቲ፣ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት እና ብልፅግና ፓርቲ ተሳትፈዋል።


 

የክርክር መድረኩን አምስቱ የቦርዱ ሥራ አመራር አባላት በተገኙበት የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በይፋ አስጀምረውታል።

በዚሁ ወቅት የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፤ የክርክር መድረኩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጭና ፕሮግራሞቻቸውን ነጻ፣ ገለልተኛና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለህዝብ የሚያደርሱበት ነው ብለዋል።

ለዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃሳባቸውን ለህዝብ የሚያደርሱበትን ወጥ የሆነ የክርክር መድረክ ለማመቻችት በርካታ የሙከራ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቀዋል።

የክርክር መድረኩ መራጩ ህዝብ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አማራጭ ሃሳቦች በማጤን በዕውቀትና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ድምፅ እንዲሰጥ ማድረግ የሚስችል መሆኑን ገልጸዋል።


 

በምርጫ ክርክር የዝግጅት ምዕራፉ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጫቸውን ለህዝብ የሚያደርሱባቸው ርዕሰ ጉዳዮች በገለልተኛ ሙያተኞች ጥናት መካሄዱንም አስታውሰዋል።

በተጨማሪም በክሩክሩ ወቅት የሚቀርቡ አሃዛዊ መረጃዎችና ሀሳቦች ትክክለኝነት የሚመዝኑና የሚያጣሩ ባለሙያዎች እንዲካተቱ መደረጉንም አንስተዋል።

በክርክር መድረኩም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እንዲገኙ በማድረግ ለዲሞክራሲ ምኅዳር መጎልበት ከፍተኛ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አካታችነተና አሳታፊነትን ለማረጋገጥ የሚደረጉ የድጋፍና ክትትል ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ መራጩ ህዝብ በቀረቡት የማኑዋልና ዲጂታል አማራጮች ድምፅ መስጠት የሚያስችለውን ካርድ በስፋት እየወሰደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የክርክር መድረኩም መራጩ ህዝብ ድምፅ መስጫ ካርድ እንዲወስድ ከፍተኛ መነቃቃት እንደሚፈጥር ሰብሳቢዋ ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም