ቀጥታ፡

የሐሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግርን ለመግታት በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ የቁጥጥር ሥርዓት እየተዘረጋ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2018(ኢዜአ)፦ የሐሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግርን ለመግታት በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ የቁጥጥር ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን አስመልክቶ በወጣው ዓመታዊ ሪፖርት ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ለውጡን ተከትሎ የሀሳብ ነፃነት፣ ብዝሃነትና አካታችነት ተፈጥሯል፡፡

ዜጎች በተለያዩ አማራጮች መረጃ የሚያገኙበትና ሀሳባቸውን በነጻነት የሚያንሸራሽሩበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።

ይህንን መልካም ዕድል በአዋጅና በመመሪያ በመደገፍ ለዴሞክራሲና ለሀገር ግንባታ ለማዋል እየተሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

ባለስልጣኑ ከሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር ስርጭት ጋር በተያያዘ በተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጥናት ሲያደርግ ቆይቷል ነው ያሉት፡፡

የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ለብሔራዊ ደህንነትና ለሀገር ሰላም፤ ለብዝሀነትና እኩልነት እንዲሁም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አደጋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ባለፉት ዓመታት የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል ጥናት በማካሄድ የመፍትሄ እርምጃ ሲወሰድ ቆይቷል ብለዋል፡፡

ባለስልጣኑ በተሰጠው ሃላፊነት መሰረት ማህበራዊ ሚዲያዎች የጥላቻ ንግግር እና የሀሰት መረጃዎችን ሪፖርት በቀረበላቸው በ24 ሰዓት ውስጥ እንዲያነሱ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በዘንድሮ ዓመት ከጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ጋር በተያያዘ የማህበራዊ ሚዲያዎች ግዴታና ሃላፊነታቸውን የተወጡበትን መንገድ የሚያሳይ ሪፖርት መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡

ዓመታዊ ሪፖርቱ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተከታይ ባላቸውና ከፍተኛ ይዘት በሚሰራጭባቸው አምስት የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገፆች ትኩረት ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በአምስት ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች በቴክኖሎጂ በታገዘ የህዝብ አስተያየት መጠይቅ ተሰብስቦ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መተንተኑን ገልጸዋል፡፡

በተለይ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ታግዘው የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ይዘቶች ስጋት መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዘው በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ ይዘቶች በሀገር ሰላምና ልማት፣ በዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ላይ ስጋት እንዳይፈጥሩ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩም አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም