በውጭ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ቅርሶችን የማስመለሱ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
በውጭ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ቅርሶችን የማስመለሱ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤መጋቢት 18/2018 (ኢዜአ)፦በውጭ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ቅርሶችን የማስመለሱ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ገለጸ።
ባለስልጣኑ በመቅደላ ጦርነት ጊዜ ከመቅደላ ተዘርፎ ከ150 አመታት በላይ ያስቆጠረውን ከወርቅ የተሰራ የአፄ ቴዎድሮስ ባለቤት የእቴጌ ጥሩወርቅ ውቤ የፀጉር ጌጥ ( ወለባ) የኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር አባላት፣ እና ሌሎች አካላት በተገኙበት የርክክብ መርሃ ግብር አካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እንደተናገሩት፤ ባለፉት ዓመታት በውጭ ሀገራት የሚገኙ ቅርሶችን የማስመለስ ስራዎች በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
ከ72 በላይ ቅርሶችን በበጎ ፍቃደኝነት፣ በትብብርና በድርድር ማስመለስ መቻሉን ገልጸው፤ ለሀገር ውስጥና ውጭ ጉብኚዎች እንዲበቁም ተደርጓል ብለዋል።
ከውጭ ሀገራት የተመለሱ ቅርሶችን የሚታዩበት ክፍል የማዘጋጀት ስራዎችን እስከ ሰኔ 2018 ዓም ድረስ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በውጭ ሀገራት በርካታ ቅርሶች የሚገኙ በመሆኑ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የሚሰሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
በውጭ ሀገራት የሚገኙ የሚታወቁ ቅርሶችን ቆጠራ ማድረግ፣ መመዝገብና ዲጂታላይዝ በማድረግ የማስመለስ ጥረቱን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለ አደራ ኮሚቴ የቦርድ አባል አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) የእቴጌ ጥሩወርቅ ውቤ የፀጉር ጌጥ ላይ ቅርሱ እ.ኤ.አ 1868 ከመቅደላ እንደተወሰደ በጽሁፍ መስፈሩን ይናገራሉ።
ይህም ቅርስ ጣሊያን ሮም ላይ ለጨረታ ቀርቦ ጨረታውን በአጭር ጊዜ ማስቆም መቻሉን ነው የገለጹት።
ቅርሱ ትልቅ ታሪክ ያለው መሆኑን ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመስራት ለማስመለስ መቻሉን አብራርተዋል።
የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን ቅርሶች ለማስመለስ መተባበርና የበለጠ በጋራ በመሰራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ለትውልዱ የሀገሪቱን ትልቅነት ታሪክ ለማስተማር ቅርሶች ጉልህ አሰተዋጽኦ እንዳላቸውም ገልጸዋል።