ቀጥታ፡

መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የሰጠው ከፍተኛ ትኩረት የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም አሳድጓል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2018(ኢዜአ)፦ መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሰጠው ከፍተኛ ትኩረትና እያደረገ ያለው ድጋፍ የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ማሳደጉን የተለያዩ አምራቾች ገለጹ።

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በአዲስ አበባ እና በሸገር ከተማ የሚገኙ የጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ የቆዳ፣ የምግብና በኤሌክትሮኒክስ ግብዓቶች አምራች ኢንዱስትሪዎችን የመስክ ምልከታ አድርገዋል።

በመስክ ምልክታው መንግስት ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት ተጨባጭ ውጤቶችን የተመዘገቡ ሲሆን ዘርፉ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ ለተኪ ምርትና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ወሳኝ ድርሻ ያለው መሆኑ በዚሁ ወቅት ተጠቁሟል፡፡

የኒው ዊንግ አዲስ ጫማና ቆዳ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ ኢቫኖ መስፍን በዚሁ ወቅት፤ ኒው ዊንግ አዲስ ለ16 ዓመታት በቆዳና ጫማ ምርት ዘርፍ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በቆይታው ያካበተውን ልምድ ተጠቅሞ ያመረታቸውን ምርቶች ለሰሜን አሜሪካ ገበያ በስፋት እያቀረበ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

በዘርፉ በዓለም ላይ ካሉ ግዙፍ ኩባንያዎች ጋር ተወዳዳሪ መሆን የቻልነው በመንግስት በኩል ለላኪዎች የሚደረገው የፋይናንስና የሎጂስቲክስ ድጋፍ በመኖሩ ነው ብለዋል።


 

ቡም ማኑፋክቸሪንግ የተባለ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ፀጋ ደበበ በበኩላቸው፤ ድርጅታቸው የተለያዩ ማቀዝቀዣዎችን በማምረት በኩል ትልቅ እመርታ ማሳየቱን ተናግረዋል።

 


 

በተለይም ከውጭ የሚመጡ ቴክኖሎጂዎችንና ዕውቀቶችን በሀገር ውስጥ በማስረጽ ውጤታማ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

እስካሁን ለ400 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ተናግረው፤ መንግስት እያደረገ ያለው ድጋፍ በተኪ ምርት ላይ ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጡ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡


 

የቦኤዝ የምግብ ኮምፕሌክስ ባለቤት ዮሴፍ ታደሰ በበኩላቸው መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ትልቅ መነቃቃት መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

በተለይም በግብርናው ዘርፍ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገው ጥረት ለፋብሪካቸው ግብዓት በማቅረብ በኩል ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቁመዋል።

መንግስት በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና ለማስፋፊያ የሚሆን መሬት ለማመቻቸት እያደረገ ያለው ድጋፍ የምርት አቅማቸውን ይበልጥ እያጠናከረ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም