በመዲናዋ ተረጂነትን በመቅረፍ ዜጎች በሀገር ግንባታ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ለማድረግ በተሰሩ ስራዎች ውጤቶች ተመዝግበዋል - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ ተረጂነትን በመቅረፍ ዜጎች በሀገር ግንባታ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ለማድረግ በተሰሩ ስራዎች ውጤቶች ተመዝግበዋል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2018(ኢዜአ)፦ በመዲናዋ ተረጂነትንና ጥገኝነትን በመቅረፍ ዜጎች በሀገር ግንባታ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ለማድረግ በተሰሩ ስራዎች ውጤቶች መመዝገባቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማዋ በምግብ ዋስትና እና ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም በርካታ ተጠቃሚዎችን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በማሸጋገር ዛሬ መርቀዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፤ ባለፉት ጥቂት አመታት ከ695ሺህ በላይ ዝቅተኛ እና ምንም ገቢ ያልነበራቸው ዜጎችን በሴፍትኔት ፕሮግራም በማካተት ከተረጂነት ወደ አምራችነት ማሸጋገር ተችሏል ብለዋል፡፡
እነዚህ ወገኖች በአሁኑ ወቅት ከራሳቸው አልፈው ቤተሰቦቻቸውንና ሀገራቸውን መርዳት መጀመራቸውን ጠቁመው የዛሬ ተመራቂዎችም በየአካባቢያቸው ተለይተው በተለያዩ ድርጅቶች የስራ ላይ ልምምድ ሲያደርጉ የቆዩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህ ፕሮግራም ወጣቶችን ራሳቸውን በማስቻል የምግብ ዋስትናንና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረገው ሀገራዊ ጥረት አካል መሆኑን ገልጸዋል።
ወጣቶቹ በስልጠና ቆይታቸው የህይወት ክህሎትን ጨምሮ የተለያዩ የሙያ ስልጠናዎችን እንዳገኙ ገልጸው ከተረጅነት ወደ አምራችነት ለሚደረግው ሽግግር ትልቅ አቅም እንደሚሆኑም ጠቁመዋል።
ተረጂነትንና ጥገኝነትን በማስቀረት ዜጎች በሀገር ግንባታ ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማድረግ በተሰሩ ስራዎች ውጤቶች መመዝገባቸውን ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡
የስራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም ወጣቶችን ከተረጂነት ስሜት አውጥቶ ወደ ምርታማነት እያሸጋገር እንደሚገኝና ወጣቶች ለመቀጠርም ሆነ በራሳቸው ስራ ፈጥረው ለመስራት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርላቸው ገልጸዋል፡፡
ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የሚደረገው ሽግግር ብልጽግናን ፈጥኖ እውን በማድረግ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አይነተኛ ሚና እንደሚጫዎትም አመላክተዋል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ ሚሊዮን ማቲዎስ፤ የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራሙ ወጣቶች ለሀገር ኩራት ወደሚሆኑበት ደረጃ አሸጋግሯቸዋል ብለዋል፡፡
ከሰልጣኞች መካከል ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ፎዚያ አወል፣ ነጻነት እና አሸብር እንዳሻው፤ በመረጥነው የስራ ሙያ ሰልጥነን አሁን ላይ ከቤተሰብ ጥገኝነት ተላቀን የራሳችን ገቢ መፍጠር ችለናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡