ቀጥታ፡

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት ለመሳተፍ ተዘጋጅተናል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2018(ኢዜአ)፦ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

በዚህም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን ያስመዘገቡ ሲሆን፤ ሌሎች አስፈላጊ የምርጫ ቅድመ ዝግጅቶችም እየተከናወኑ ይገኛሉ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ወጣቶች እንደገለጹት፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት በዝግጅት ላይ ናቸው።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወጣት መዲና መሀመድ ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ምርጫዎች ላይ በመሳተፍ እንደ ዜጋ ለዴሞክራሲ ባህል ግንባታ የሚጠበቅባትን ድርሻ መወጣቷን ገልጻለች።

ዘንድሮ በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የመራጭነት ካርድ ማውጣቷን ገልጻ፤ የወጣቱን ተጠቃሚነት ያረጋግጣል የምለውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅቻለው ብላለች።

ወጣት ኤርሚያስ ወንድሙ በበኩሉ፤ በምርጫው ወጣቱን ጨምሮ የዜጎችን ተጠቃሚነት ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገር ለሚሰራ ፓርቲ ድምጽ ለመስጠት ተዘጋጅቻለሁ ሲል ገልጿል።

የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚችለውን ፓርቲ ለመምረጥ የመራጭነት ካርድ ወስዶ በመጠባበቅ ላይ መሆኑን የተናገረው ደግሞ ወጣት ኢሳ ሰኢድ ነው፡፡

ሌላኛዋ ወጣት የተመኝ አስማማው በበኩሏ፤ ምርጫው የዲሞክራሲ መብት ተጠቃሚነትን የምናረጋግጥበት መንገድ በመሆኑ ያስተዳድረኛል የምለውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ ብላለች፡፡


 

የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ፕሬዚዳንት በረከት ቢርቢርሳ፤ ማህበሩ ከዚህ ቀደም በነበሩ ምርጫዎች ላይ ወጣቶች የተሻለ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የማስተባበር ሚናውን ሲወጣ መቆየቱን አንስቷል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም ለወጣቶች የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ በመስራት በምርጫው አስተዋጿቸውን እንዲያበረክቱ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም