ቀጥታ፡

ጥራቱ የተረጋገጠ መድኃኒት ለማኅበረሰቡ የማቅረብ ሥራ እየተከናወነ ነው

አርባምንጭ፤ መጋቢት 18/2018 (ኢዜአ)፡- ጥራትና ፈዋሽነታቸው የተረጋገጡ መድኃኒቶችን ለማኅበረሰቡ የማቅረብ ሥራ በልዩ ትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

8ኛው የጤና ዘርፍ የባለድርሻ አካላት ምክክር መድረክ በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።



 
የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ፍሬሕይወት አበበ በዚሁ ወቅት፤ የአሠራርና የአደረጃጀት ሥራዎችን በማሻሻል የመድኃኒት አቅርቦት ጥራትና ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ ነው ብለዋል።

መድኃኒቶችን በተገቢው መንገድ መጠቀም በተለይ መድኃኒት የተላመዱ በሽታዎች የሚያደርሱትን ጫና ለመቀነስ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አስገንዝበዋል።

ከ53 ሺህ በሚልቁ የጤና ተቋማት ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ የመድኃኒት አቅርቦት ሥርዓት እንዲኖር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።


 

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አብዱልቃድር ጋልጋሎ (ዶ/ር) ፈዋሽነቱና ደኅንነቱ የተረጋገጠ መድኃኒት ለማኅበረሰቡ እንዲዳረስ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሲሠራ መቆየቱን ጠቅሰው፤ በዲጂታል ሥርዓት በመታገዝ አቅርቦቱን ይበልጥ ለማሳለጥ እንደሚሠራ አመላክተዋል።


 

በበጀት ዓመቱ ያለፉት ወራት 64 ቢሊየን ብር የሚገመቱ መድኃኒቶችና የሕክምና መገልገያዎች ለጤና ተቋማት መሰራጨታቸውንም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም