ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በሰላም ማስከበር ዘርፍ ያላቸውን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት የሚያጠናክር ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በሰላም ማስከበር ዘርፍ ያላቸውን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት የሚያጠናክር ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፤መጋቢት 18/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ በሰላም ማስከበር ዘርፍ ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር ወደ ስልታዊ አጋርነት ማሳደግ ያለመ የሁለትዮሽ ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ (ኢ/ር) እና በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲ ላሜክ ፈርመዋል፡፡
ስምምነቱ በዋናነት በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ የሚሰማሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላትን ኦፕሬሽናል ዝግጁነት ለማሳደግና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ብቃት ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ነው።
በስምምነቱ መሰረት፣ የዓለም አቀፍ የሰላም ድጋፍ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት (IPSTI) እና የኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት (CTS) የሚሰጡ የሥልጠና ሰርተፊኬቶች ዓለም አቀፍ ዕውቅና እና የምርምር ተግባራት ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ይደረጋል።
በተጨማሪም ስምምነቱ የኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ማዕከል የሚሰጡ የስልጠና ሰርተፊኬቶች በተባበሩት መንግሥታትና በአፍሪካ ሕብረት ዘንድ የላቀ ዕውቅናን ያላቸው እንዲሆኑ ማስቻልን እንደ ግብ ማስቀመጡ ተመላክቷል።
ለዚህም ስኬት የፈረንሳይ መንግስት አስፈላጊውን የቴክኒክና የማቴሪያል ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን፣በተለይም ሰላም አስከባሪዎች በጦር ሜዳ የሚያጋጥሟቸውን የፈንጂ አደጋዎች የመከላከል አቅማቸውን ማሳደግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል።
ይህ ስምምነት በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ጠንካራ ወታደራዊ ዲፕሎማሲ መሠረት ያደረገ ነው።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ያላት ቀዳሚ ተሳትፎና አሁንም በሰላም አስከባሪ ብዛት ከዓለም ቀዳሚዎቹ ተርታ መሰለፏ ለትብብሩ መጠናከር በምክንያትነት ተጠቅሷል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላምና ደህንነት የምታበረክተውን አስተዋፅኦ ይበልጥ ውጤታማ እንደሚያደርገው ተገልጿል።
በተጨማሪም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ዘላቂ ወዳጅነት ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው መገለጹን ኢዜአ ከመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።