ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት የልጅነት ልምሻ ክትባት እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት የልጅነት ልምሻ ክትባት እየተሰጠ ነው
ቦንጋ፣ ደብረ ብርሃን፤ መጋቢት 18/2018 (ኢዜአ)፦ 5ኛው ዙር የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) ክትባት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ዛሬ መሰጠት ጀምሯል።
በዚህም መሠረት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ኢብራሂም ተማም በቦንጋ ከተማ ሸታ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው የክትባት ዘመቻውን አስጀምረዋል።
በዚሁ ወቅትም መንግሥት የበለጸገና ጤናማ ዜጋን ለመፍጠር ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል አንዱ የክትባት አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ነው ብለዋል።
ክትባት ሕጻናት በአዕምሮና በአካል ጤናማ እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለው ገልጸው፤ ይህም በመደበኛና በዘመቻ መልክ እየተካሄደ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ከፖሊዮ ክትባት በተጨማሪ የአፈጣጠር ችግር ያለባቸውን ሕጻናት፣ ከወሊድ ጋር የተያያዘና ፌስቱላን የመሳሰሉ ችግሮች ያሉባቸው እናቶች ልየታና ወደ ሕክምና የመላክ ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ስሜነህ አያሌው ደግሞ በደብረ ብርሃን ከተማ የፖሊዮ ክትባትን አስጀምረዋል።
የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻውን ለመስጠት 12 ሺህ 501 ባለሙያዎችን በማሳተፍ በትምህርት ቤቶች፣ በቤት ለቤትና በጤና ተቋማት መሰጠት መጀመሩን አስታውቀዋል።
ማኅበረሰቡም በአካባቢው የሚገኙ ሕጻናትን በማስከተብ ከበሽታው ለመጠበቅ የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝ ጠይቀዋል።