ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክር መድረክ ማካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2018(ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያዘጋጀው የክርክር መድረክ መጪው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ይበልጥ አካታችና አሳታፊ እንዲሆን ለማድረግ ያለመ የመጀመሪያውን የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ክርክር ነው።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ቦርዱ ባለፉት ጥቂት ወራት የክርክር መድረኩን ለማዘጋጀት ሲሰራ የቆየ ሲሆን፤ ይህም በኢትዮጵያ የምርጫ ሂደት ውስጥ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው ብለዋል።


 

ይህ ተነሳሽነት የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን አማራጭ የፖሊሲ ሃሳቦች ለሕዝብ የሚያቀርቡበት ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረው፤ ፓርቲዎቹ አቋማቸውን ለማሳወቅ እንደሚረዳና መራጩ ሕዝብ ያደገ ግንዛቤ እንዲኖረው አስቻይ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።

እንደ ሰብሳቢዋ ገለጻ፤ ቦርዱ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለመደገፍ የተለያዩ ስልጠናዎችን ጨምሮ ፓርቲዎች የሙከራ ክርክሮችን እንዲያካሄዱ የሚያስችል ዕድልንም ፈጥሯል።

መድረኩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮችን እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን በማገናኘት ለዲሞክራሲያዊ ምህዳር መስፋት አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም አብራርተዋል።


 

የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ እንደገለጹት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክር መድረክም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ይበልጥ አካታች እና አሳታፊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ እያደረገ ያለው ጥረት አካል ነው።

Ethiopian News Agency #ኢዜአ #ምርጫ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም