ጣልያን ዴንማርክ እና ስዊድን ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የጥሎ ማለፍ ፍጻሜ አለፉ - ኢዜአ አማርኛ
ጣልያን ዴንማርክ እና ስዊድን ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የጥሎ ማለፍ ፍጻሜ አለፉ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2018 (ኢዜአ)፦ የ23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ የአውሮፓ ዞን የመጀመሪያ ዙር የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ማምሻውን ተደርገዋል።
በቤርጋሞ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ጣልያን ሰሜን አየርላንድን 2 ለ 0 አሸንፋለች።
ሳንድሮ ቶናሊ እና ሞይስ ኪን ጎሎቹን አስቆጥረዋል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ዴንማርክ ሰሜን ሜቄዶናያን 4 ለ 0 ረታለች።
በፓርከን ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ጉስታቭ ኢሳክሰን ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ሚኬል ዳምስጋርድ እና ክርስቲያን ኖርጋርድ ቀሪዎቹን ጎሎች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ስዊድን ዩክሬንን 3 ለ 1 አሸንፋለች።
በቫሌንሺያ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ የአርሰናሉ አጥቂ ቪክቶር ዮኮሬሽ ሁለት ግቦችን በጨዋታ ቀሪውን ጎል በጨዋታ በማስቆጠር ሀትሪክ ሰርቷል።
ማትቪይ ፖኖማሬንኮ ለዩክሬን ብቸኛውን ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ፖላንድ በሮበርት ሎዋንዶውስኪ እና ፒተር ዚሊኒሲኪ ጎሎች አልባኒያን 2 ለ 1 አሸንፋለች።
አርበር ሆክስሃ ለአልባኒያ ብቸኛውን ጎል አስቆጥሯል።
በሌሎች ጨዋታዎች ኮሶቮ ስሎቫኪያን 4 ለ 3 ስትረታ ቼክ ሪፐብሊክ አየርላንድን፣ ቦሲኒያ እና ሄርዞጎቪና ዌልስን በተመሳሳይ በመለያ ምት አሸንፈዋል።
ውጤቶቹን ተከትሎ ጣልያን፣ ዴንማርክ፣ ስዊድን፣ ፖላንድ ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ቦሲኒያ እና ሄርዞጎቪና እንዲሁም ኮሶቮ ለፍጻሜ ጨዋታ አልፈዋል።
ዛሬ አስቀድሞ በተደረገ ጨዋታ ቱርኪዬ ሮማንያን 1 ለ 0 አሸንፋለች።
ጣልያን ከቦሲኒያ እና ሄርዞጎቪና፣ ፖላንድ ከስዊድን፣ ቱርኪዬ ከኮሶቮ እና ዴንማርክ ከቼክ ሪፐብሊክ መጋቢት 22 ቀን 2018 ዓ.ም ለዓለም ዋንጫው ለማለፍ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በጥሎ ማለፉ የሚያሸንፉ አራት ሀገራት አስቀድመው በቀጥታ ወደ ዓለም ዋንጫ ያለፉ 12 የአውሮፓ ሀገራትን ይቀላቀላሉ።