ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ካርድ በማውጣት የሚበጃቸውን ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2018 (ኢዜአ)፡- ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጭነት ካርድ በማውጣት ለሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚሠራ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ተናገሩ።

እጸገነት ሙሉጌታ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የሀገርንና የትውልድን ተስፋ ብሩኅ ለማድረግ ሴቶች በምርጫ ወቅት የሚያደርጉት ንቁ ተሳትፎ የጎላ ሚና አለው።

ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጭነት ምዝገባ ማከናወናቸውንም ተናግረዋል።

ማኅሌት ጥላሁን በበኩላቸው፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን መጠቀም የሚያስችሉ ዕድሎችን ያሰፋና የሕዝቦችንም ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በር የከፈተ ነው ብለዋል።

ይበጀኛል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸው፤ ዜጎች በምርጫ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ይመክራሉ።

ሴቶች ለተሻለ ነገ በምርጫው ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይገባናል ያሉት ደግሞ ዝናሽ ቦጋለ ናቸው።

ምርጫ ዴሞክራሲያዊ መብታችንን የምናረጋግጥበት መንገድ በመሆኑ የምርጫ ካርዳችንን ወስደናል  ያሉት ደግሞ ሰናይት ቀበታ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም