የጥፋት ኃይሎችን በመታገል የልማት ዕቅዶችን ለማሳካት መረባረብ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የጥፋት ኃይሎችን በመታገል የልማት ዕቅዶችን ለማሳካት መረባረብ ይገባል
ወልዲያ፤ መጋቢት 18/2018 (ኢዜአ)፡- ለግጭት የሚጥሩ የጥፋት ኃይሎችን በመታገል የዘላቂ ሰላምና ልማት ዕቅዶቻችንን ለማሳካት መትጋት አለብን ሲሉ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ገለጹ።
ምክትል ርዕሰ መሥተዳድሩ በሰሜን ወሎ ዞን ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተዋል።
በዚሁ ወቅትም ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት በመሆኑ የጋራ አጀንዳችን ሆኖ እየተሠራበት ነው ብለዋል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ (ዶ/ር)።
ለሰላምና የልማት ሥራዎች የጸጥታ አካላት ብርቱ ጥረት እንዳለ ሆኖ፤ የሕብረተሰቡ ትብብርና ተሳትፎ ከፍተኛ ሚና እንዳለም አስገንዝበዋል።
በመሆኑም ለግጭትና ጦርነት የሚጥሩ የጥፋት ኃይሎችን በመታገል የዘላቂ ሰላምና ልማት ዕቅዶቻችንን ለማሳካት በጋራ መትጋት አለብን ብለዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር፤ የዞኑ ሕዝብ የሰላም ጥረትና ለልማት ያለው ትጋት የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።
የጥፋት ዓላማ ይዘው ይንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች መንግሥት ባቀረበላቸው የሰላም ጥሪ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ መመለሳቸውን ገልጸው፤ በዚህ ጥረት ውስጥ የሕዝቡ እገዛ የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም በየአካባቢው የሀገርን ጥቅም አሳልፈው ለመስጠት የሚንቀሳቀሱ ባንዳዎችን በጋራ መታገል እንደሚገባ አመላክተዋል።