በኦሮሚያ ክልል በበልግ እርሻ እስካሁን 680 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል በበልግ እርሻ እስካሁን 680 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል
አዲስ አበባ፣መጋቢት 18 /2018(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው የበልግ እርሻ ወቅት እስካሁን 680 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያየ የሰብል ዘር መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ በክልሉ በዘንድሮው የበልግ ወቅት 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማልማት ከ46 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።
በክልሉ በልግ አብቃይ በሆኑ 11 ዞኖች እየተከናወነ ባለው በዚህ ስራ እስካሁን 1 ነጥብ 79 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መታረሱን ገልጸዋል።
ከታረሰው መሬት ውስጥ 680 ሺህ ሄክታር የሚሆነው በኩታ ገጠም የአመራረት ዘዴ ዘር መሸፈኑን ገልጸው፥ ከአጠቃላይ ሊለማ ከታቀደው መሬት ውስጥ 884 ሺህ ሄክታር የሚሆነው በትራክተር የታረሰ መሆኑ ተናግረዋል።
የበልግ ዝናብ በመልካም ሁኔታ እየዘነበ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፣ ለአርሶ አደሩ የሚያስፈልጉ የግብዓት አቅርቦቶች በወቅቱ እንዲደርሱ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
ከግብዓት አቅርቦት አንጻር ከ600 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያና፣ 188 ሺህ ኩንታል የተለያየ ሰብል ዘር ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ ይገኛል ብለዋል።
በልማቱ ድርቅን መቋቋም የሚችሉና በፍጥነት ምርት የሚሰጡ እንደ ማሾ፣በቆሎ፣ ቦሎቄ፣ ማሽላ፣ስንዴ፣ገብስና አተር ያሉ ሰብሎች በስፋት እየለሙ መሆኑንም አመልክተዋል።
ልማቱ በስፋት እየተከናወነባቸው ከሚገኙ አካባቢዎች መካከል ምስራቅ እና ምዕራብ ሀረርጌ፣ ባሌ እና ምስራቅ ባሌ፣ ጉጂ፣ ምስራቅ ቦረና፣ አርሲ እና ምስራቅ ሸዋን ጨምሮ 11 ዞኖችን ጠቅሰዋል።
ለሥራው ስኬታማነት በአርሶና አርብቶ አደሩ ዘንድ የክህሎት ስልጠና መሰጠቱንና የሙያ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን አቶ ጌቱ ገልጸዋል።
በክልሉ ለበልግ አዝመራ የሚሆን በቂ የማዳበሪያ ክምችት መኖሩን የገለጹት ኃላፊው፣አርሶ አደሩ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የእርሻ ሥራውን በወቅቱ እንዲያከናውንም አሳስበዋል።