ቀጥታ፡

ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊነት መገናኛ ብዙኃን ድርብ ኃላፊነት አለባቸው  

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2018 (ኢዜአ)፡- 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሐዊ ዴሞክራሲያዊና ሠላማዊ ሆኖ እንዲካሄድ በሚደረገው እንቅስቃሴ መገናኛ ብዙኃን ድርብ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተገለጸ።     

የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር ብሩክ ኃይሉ (ፕ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ የመገናኛ ብዙኃን ሚና የማይተካ ነው።      
 
ምርጫው የዲሞክራሲ ልምምድና ባህል ከፍ ወዳለ ደረጃ የሚሸጋገርበት እንደሚሆን ይጠበቃል ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ በዚህ ረገድ የመገናኛ ብዙኃን ድርሻ የላቀ ነው ብለዋል።     
 
መራጩ ስለሚመርጠው ፓርቲ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው፤ ፓርቲዎች በተለያዩ ዘርፎች ያሏቸውን አማራጭ ሐሳቦች ለሕዝቡ በአግባቡ እንዲያስተዋውቁ መገናኛ ብዙኃን ዕድል መፍጠር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።     
 


 

ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በበኩላቸው መገናኛ ብዙኃን የምርጫ ዘገባዎች ላይ ለባለሙያዎቻቸው የክኅሎት ሥልጠናዎችን በበቂ ደረጃ ሊሰጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።    
 
ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን ዐቅም መገንባት ወሳኝ ነው ብለዋል።  
 
የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በኤዲቶሪያል ፖሊሲዎቻቸው ላይ የተቀመጡ ሂደቶችን ተከትሎ በመሥራት፤ ለምርጫው ስኬት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።  


  
 
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የመካከለኛው ምሥራቅ፣ ኤዥያ እና ፓስፊክ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪና የፖሊሲ ጥናት ባለሙያ አንተነህ ጌታቸው፤ ጋዜጠኞች የምርጫ ሕጉን፣ አዋጆችና የተሻሻሉ ሕጎች ላይ በቂ ግንዛቤ ሊጨብጡ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም