ቀጥታ፡

የትግራይ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2018 (ኢዜአ) ፦ የትግራይ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት ከመጋቢት 23 እስከ 25 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በትግራይ ክልል የሚከናወነውን የምክክር ሂደት አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በመግለጫቸው፤ ኮሚሽኑ እስካሁን ሂደቱን አሳታፊ እና አካታች ለማድረግ ሲያከናውናቸው የቆዩ ስራዎች ስኬታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ስራዎቹም ከወረዳ ጀምሮ ህዝብን ባሳተፈ መልኩ ሲከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል የሚገኙ ዜጎች በምክክር ሂደቱ የመሳተፍ ሙሉ መብት እንዳላቸውና ለሂደቱ ውጤታማነትም በጎ አበርክቶ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል የምክክር ሂደቱን ለመጀመርና ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ሰፊ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ዋና ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው አስታውሰዋል።

በዚህም ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀሌ እና በአዲስ አበባ ከ22 ጊዜ በላይ ውይይቶች መደረጋቸውን ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ በእነዚህ ጥረቶች ውስጥ በክልሉ ውስጥ ሂደቱን ለማካሄድ የሚያስችሉ አስቻይ ሁኔታዎች ባለመፈጠራቸው፤ የአጀንዳ ማሰባሰብና የተወካዮች ምርጫ ሂደቱ በአዲስ አበባ እንዲከናወን መወሰኑን አስረድተዋል።

በዚህም በክልሉ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት ከመጋቢት 23 እስከ 25 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

ሁሉም በየደረጃው የሚገኙ የባለድርሻ አካላት ከመጋቢት 23 ጀምሮ በሚከናወነው በዚህ ሂደት ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

Ethiopian News Agency #ኢዜአ #ምክክር

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም