ዕድሜያቸው ደርሶ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚመርጡ ወጣቶች ምን አሉ? - ኢዜአ አማርኛ
ዕድሜያቸው ደርሶ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚመርጡ ወጣቶች ምን አሉ?
በኢትዮጵያ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለማካሄድ፤ ብሔራዊ ምርጫ ቦረድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የቅድመ ምርጫ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል።
ኢትዮጵያውያንም የሚፈልጉትን ፓርቲ ወይንም የግል ተወዳዳሪ ለመምረጥ የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ እየሰወዱ ነው።
ዕድሜያቸው ደርሶ የምርጫ ካርድ ወስደው ለመጀመሪያ ጊዜ ዘንድሮ በመራጭነት ለመሳተፍ የተዘጋጁ የድሬዳዋ ወጣቶችን ኢዜአ አነጋግሯል።
ወጣት ነሲማ ቶፊቅ ዕድሜዬ ደርሶ ፖለቲካዊ መብቴን ለመጠቀም በመብቃቴ ደስ ብሎኛል፤ የመጀመሪያ የምርጫ ተሳትፎየን ለማድረግ ድምፅ መስጠት የሚያስችለኝን ካርድ ይዣለሁ ብላለች።
የወደፊቷ ኢትዮጵያ የምትወሰነው ዛሬ በምናደርገው ልማትና አጠቃላይ የፖለቲካ ተሳትፎ ነው ያለችው ወጣቷ፤ ተሳትፏችን ጥቅሙ ለሀገራችን በመሆኑ ዕድሉ ሊያመልጠን አይግባም ትላለች።
ወጣት ራህማ ጀማል በበኩሏ፤ በመራጭነት ለመሳተፍ የመጀመሪያዋ በመሆኑ ልዩ ስሜት እንዳሳደረባት ትናግራለች።
የምርጫ ካርድ መያዟን ገልፃ ሌሎች ወጣቶችም የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መክራለች።
ለመራጭነት የሚያበቃትን ካርድ መውሰዷን የገለጸችው ወጣት ሙክራብ ካሳዬ በበኩሏ፤ ለምርጫው ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ እንደ ዜጋ የበኩሏን ለመወጣት መዘጋጀቷን ትገልጻለች።
ወጣት መሐመድ አብደላ፤ የዘንደሮው ምርጫ ከእኛ ጋር ተቀራራቢ ዕድሜ ላይ ለሚገኙ ወጣቶች ታሪካዊ በመሆኑ በመራጭነት ለመሳተፍ ተዘጋጅተናል ብሏል።
እርሱ እና ጓደኞቹ የምርጫ ካርድ ወስደው የድምጽ መስጫውን ቀን እየጠበቁ መሆናቸውን ተናግሯል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶች ምክርቤት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አማረ ጥላሁን፤ ዕድሜያቸው የደረሱ ወጣቶች የምርጫ ካርድ በመውሰድ፣ ለምርጫው ሰላማዊ ሂደት በማስተባበር እና ለመመረጥ መስፈርቱን የሚያሟሉ ወጣቶችም በዕጩነት የቀረቡ እንዳሉ አስረድቷል።