ሸገር ከተማን ምቹ የቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሸገር ከተማን ምቹ የቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው
ሸገር፤ መጋቢት 18/2018 (ኢዜአ)፦ ሸገር ከተማን ምቹ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የሚያስችሉ ጥረቶች እየተከናወኑ መሆኑን የከተማዋ ቱሪዝም ኮሚሽን አስታውቋል።
የሸገር ከተማ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ቢኒያም ጸጋዬ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በከተማው የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን በመለየት፣ በማልማትና በማስተዋወቅ ረገድ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው።
ከመዳረሻዎች ልየታ እና ልማት አንጻር በ2017 በጀት ዓመት 85 የተፈጥሮና ባህላዊ መዳረሻዎች በጥናት ተለይተው ወደ ልማት መገባቱን አውስተዋል።
የቱሪስቶችን ቆይታ ለማራዘምም የመሠረተ ልማት አቅርቦቶችን የማሟላትና የአካባቢውን ባህላዊና ተፈጥሯዊ ሀብት የመጠበቅ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከተማዋን የኮንፍረንስ ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ከክልልና ከፌዴራል ቱሪዝም ኮሚሽን ጋር እየተሠራ እንደሆነም ገልጸዋል።
600 ሔክታር መሬት በማቅረብ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በሪዞርትና በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ልማት ላይ እንዲሰማሩ እየተደረገ ነውም ብለዋል።
አሁን ደረጃቸውን የጠበቁ 21 ሆቴሎች እየተገነቡ መሆኑና በስድስት ወራት ውስጥ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ አመላክተዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች በባህላዊ ምግቦች፣ አልባሳት፣ የእጅ ጥበብና መስተንግዶ ዘርፎች ስልጠና እንዲያገኙ ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለበርካታ የአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩንና በቀጣይም ዘርፉ ሲያድግ ተጠቃሚነታቸው ይበልጥ እንደሚሰፋ ኮሚሽነሩ አረጋግጠዋል።