የስፖርት እንቅስቃሴ ባህልን የቀየሩት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች - ኢዜአ አማርኛ
የስፖርት እንቅስቃሴ ባህልን የቀየሩት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች
በመዲናዋ የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳርቻ ስራዎች የከተማውን ገጽታ በመቀየር ውብ እንድትሆን እያደረጓት ይገኛሉ።
በዚህም በርካታ መዝናኛ ስፍራዎችና ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ነው።
እነዚህ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ቀንም ሆነ ማታ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሏቸው መሰረተ ልማቶች ተሟልተውላቸው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ያገኘናቸው ወጣቶች ለኢዜአ እንዳሉት፤ ማዘውተሪያዎቹ በጀመሩት የምሽት አገልግሎት ከስራ መልስ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ጤናችን እንድንጠብቅ አስችሎናል።
በከተማው የምሽት አገልግሎት መስጠት ከጀመሩት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መካከል በየካ ክፍለ ከተማ የሚገኝ 28 ሜዳ አንዱ ነው።
በሜዳው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ ወጣቶች መካከል ያሬድ ስጦታው ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ለበርካታ ዓመታት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት ሜዳ መሆኑን ገልጿል።
ሜዳው ከዚህ ቀደም ጥራቱን ያልጠበቀና ምንም ዓይነት እድሳት ያልተደረገለት እንደነበርም ያስታውሳል።
አሁን ግን ሜዳው ጥራቱን የጠበቀና ምሽትን ጨምሮ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሰረተ ልማት ተሟልቶለት እስከ ምሽት እስከ 4 ሰዓት እንድንጫወት አስችሎናል ይላል።
ወጣት ዳዊት ደማሙና አቤል ነጋሲ በበኩላቸው፤ የስፖርት ማዘውተሪያው የምሽት አገልግሎት መስጠት መጀመር ቀን ስራ ውለን ማታ ጊዜያችንን በስፖርት እንቅስቃሴ እንድናሳልፍ አድርጎናል ብለዋል።
ይህም ከአብሮ አደግ ጓደኞቻችን ጋር ያለን ኅብረት እንድናጎለብት አስችሎናል ይላሉ።
በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት የሚገኘው የስፖርት ማዘውተሪያም በምሽት አገልግሎት እየሰጠ ነው።
በዚሁ ወቅት ወጣት ተከተል ታዬ እንዳለው፤ ሜዳው ከዚህ ቀደም በአካባቢው ያልነበረና የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ የተገነባ ነው።
በተለይም በምሽት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሰረተ ልማቶች መያዙ ማታ ከስራ መልስ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ጤናችን እንድንጠበቅ እያስቻለን ነው ብሏል።
በዚህም ከእኩዮቹ ጋር ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት የጤና ቡድን መስርተው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጿል።
የስፖርት ማዘውተሪያው አገልግሎት ከረዥም ጊዜ በኋላ ወደ ስፖርት እንድመለስ አድርጎኛል በማለት የገለጸው ደግሞ ወጣት ማይክ ብርሃኔ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አሰግደው ኃይለጊዮርጊስ፤ በመዲናዋ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የስፖርት ማዘውተሪያ እጥረት ከመቅረፍ ባሻገር ለከተማዋ ተጨማሪ ድምቀት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የከተማዋ ወጣቶችም አልባሌ ቦታ እንዳይውሉና ጤናቸውን እንዲጠብቁ በማድረግ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የስፖርት ማዘውተሪያዎቹ የምሽት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው በተለይም ነዋሪዎች ከስራ መልስ ምቹ በሆነ ሜዳ ላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት ቦታ መኖሩ በርካታ ጥቅሞችን እያስገኘ ነው ብለዋል።
በቀጣይም የስፖርት ማዘውተሪያና መዝናኛዎችን የማስፋፋት እንዲሁም የወጣት ስብዕና መገንቢያ ማዕከላትን የማዘመን ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።