ቀጥታ፡

የሹዋሊድ በዓል አከባበር አስደናቂ ባህላዊ ትውፊቶችን ይዟል - ጎብኝዎች

ሐረር፤ መጋቢት 18/2018 (ኢዜአ)፡- የሹዋሊድ በዓል አከባበር ከሐይማኖታዊ ይዘቱ ባለፈ አስደናቂ ባህላዊ ትውፊቶችን የያዘ ነው ሲሉ የውጭ ሀገራት ጎብኝዎች ገለጹ።

የሹዋሊድ በዓል የዒድ አል-ፈጥር በዓል ከተከበረበት ቀን ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት ከተፆመ በኋላ ከስድተኛው ቀን ምሽት ጀምሮ በሐረር ከተማ በድምቀት ተከብሯል።


 

ከፈረንሳይ የመጡት ጎብኝ ግራንስ ሮቤርት አከባበሩን አስመልክተው ለኢዜአ እንዳሉት፤ እንደዚህ ዓይነት አስደናቂ ሁነቶችን ተንከባክቦ በመያዝ የዓለም ጎብኝዎች ዕድሉን አግኝተው እንዲመለከቱት ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ከቱርክ የመጡት ሱሁንዳ ኪፕሪ በበኩላቸው፤ ከእስልምና ሐይማኖት ተከታዮች ውጭ ሌሎችም ታድመውበት ሲያከብሩ መመልከታቸውን ገልጸዋል። 

ይህም ኢትዮጵያውያን አብሮነታቸው ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ ያስረዳል ነው ያሉት።


 

በሹዋሊድ በዓል አከባበር የሚያስደምም ትዕይንት መመልከታቸውን የገለጹት ደግሞ ከሰሜናዊ ካሪቢያን ከፔትሮ ሪኮ የመጡት ራፋዬል ሪቬሮ ናቸው።

በክብረ በዓሉ ላይ የታዳሚዎች አለባበስ፣ ዜማና አጠቃላይ ትዕይንቱ አስደንቆኛል ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም