የልብ ድካም መንስዔ፣ ምልክቶች እና ሕክምናው - ኢዜአ አማርኛ
የልብ ድካም መንስዔ፣ ምልክቶች እና ሕክምናው
የልብ ድካም በሽታ መንስዔ ምንድን ነው? ምልክቶቹስ? ሕክምናና መከላከያ መንገዶቹስ ምንድን ናቸው? በሚሉት ጉዳዮች ላይ በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሐኪም ዶክተር ሙህዲን አሊ (ረ/ፕሮፌሰር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ አብራርተዋል።
• የልብ ድካም በሽታ ምንድን ነው?
ዶክተር ሙህዲን እንዳሉት፤ የልብ ድካም ማለት የልብ አካል ላይ በደረሰ ጉዳት ወይም የአሠራር ለውጥ ምክንያት ለተለያዩ የሰውነት ክፍሎች የሚሠራጨው ደም በቂ ሳይሆን ሲቀር የሚከሰት የጤና መታወክ ነው።
የልብ አካል ጉዳት ሲባል የልብ ቫልቮች መጥበብ(መስፋት)፣ የልብ ደም ሥሮች መጥበብ፣ የልብ ጡንቻና ማቀፊያ መጎዳት ሊሆን ይችላል ሲሉም ያብራራሉ።
• የልብ ድካም በሽታ መንስዔ ምንድን ነው?
ከመንስዔዎቹ መካከል አንዱ ተፈጥሮሯዊ የልብ በሽታ (ከጊዜ በኋላ የሚመጣ የልብ በሽታ) ሊሆን እንደሚችልም ነው የጠቆሙት ባለሙያው።
በኢትዮጵያ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃና በተጨናነቀ አካባቢ የሚኖሩ ሕፃናት በተደጋጋሚ በቶንሲል ሕመም ይጠቃሉ፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ የተመረቱ አንቲቦዲ የተሰኙ በሽታ ተከላካዮች ከልብ ቫልቮች መጥበብ (መስፋት) ጋር ተያይዞ ለልብ ድካም ይዳርጋሉ ያሉት ዶክተር ሙህዲን፤ ይህም በሀገራችን ዋነኛ የልብ ድካም መንስዔ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ ብለዋል።
እንዲሁም ከፍተኛ የደም ግፊት፣ የልብ ጡንቻ እና የልብ ማቀፊያ በሽታ ለልብ ድካም አጋላጭ መንስዔ መሆናቸውን አመላክተዋል።
የልብ ደም ቧንቧ መጥበብ አንዱ ለልብ ድካም አጋላጭ መንስዔ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ሙህዲን፤ በዚህ መንስዔ የሚመጣው የልብ ድካም በአብዛኛው በዕድሜ በገፉ እና በወንዶች ላይ ይከሰታል ይላሉ።
አክለውም በቤተሰብ ታሪክ ተመሳሳይ በሽታ መኖር፣ ሲጋራ ማጨስ፣ ከፍተኛ ደም ግፊት፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ የስኳር በሽታ፣ የኮሊስትሮል መብዛት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ለልብ ድካም በሽታ የመጋላጥ ዕድልን እንደሚጨምር ዶክተር ሙህዲን ገልጸዋል።
• የልብ ድካም በሽታ ምልክቶች ምንድን ናቸው?
ጭንቀት፣ በቀላሉ መድከም፣ ዐቅም ማጣት፣ ያለምንም እንቅስቃሴ ወይም መጠነኛ እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ሠዓት ትንፋሽ ማጠር፣ በመኝታ ላይ ትንፋሽ ማጠር፣ ከእንቅልፍ የሚቀሰቅስ አስፈሪና ከፍተኛ የሆነ ትንፋሽ ማጠር፣ ሌሊት ላይ የሚበረታ ሳል ከምልክቶቹ መካከል መሆናቸውን አብራርተዋል።
በተጨማሪም ከልክ በላይ የልብ መምታት (የትርታ መጨመር)፣ በድንገት ራስን መሳት፣ የደረት ህመም፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ማቅለሽለሽ፣ የሆድ መነፋትና የሆድ ህመም ዋና ዋናዎቹ የልብ ድካም ምልክቶች መሆናቸውን ነው ያስገነዘቡት።
• የልብ ድካምን እንዴት መከላከል ይቻላል?
ከፍተኛ ደም ግፊትን መቆጣጠርና ሕክምና ማድረግ፣ የስኳር በሽታን መቆጣጠር፣ ሲጋራ አለማጨስ፣ የሰውነት ክብደትን መቆጣጠር፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ (ዐቅምን ያገናዘበ ቢሆን ይመረጣል)፣ ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠንን በመድኃኒት መቀነስ፣ ሕጻናት ቶንሲል ሲታመሙ እንዲታከሙ ማድረግ እንዲሁም የታዘዘን መድኃኒት ሳያቋርጡ በአግባቡ መውሰድ ለልብ ድካም ተጋላጭነትን ይቀንሳል ብለዋል።
• የልብ ድካም እንዴት ይታከማል?
እንደ ዶክተር ሙህዲን ገለጻ፤ የልብ ድካም ቀላል የሆኑ አባባሽ ነገሮችን ከማከም እስከ ከፍተኛ የልብ ቀዶ ጥገና ሕክምና ሊያስፈልገው ይችላል።
በዚህም መሠረት በቅድሚያ የልብ ድካምን ሊያባብሱ የሚችሉ ነገሮችን ማስወገድና ማከም ይገባል ይላሉ።
ለምሳሌ ይላሉ ዶክተር ሙህዲን፤ የሳንባ ምች፣ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን፣ ደም ማነስ፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ መድኃኒትን ማቋረጥ፣ እርግዝና፣ አልኮል አብዝቶ መጠጣት፣ ጨው አብዝቶ መመገብ የልብ ድካምን የሚያባብሱ ነገሮች መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩል በሐኪም የታዘዙ የልብ ድካም አጋዥ መድኃኒቶችን በታዘዘው መሠረት በተገቢው ሁኔታ መጠቀም ተገቢ መሆኑን መክረዋል።
ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ የልብ ቀዶ ሕክምና ማድረግ እንደሚቻል ጠቁመዋል።
ተመጣጣኝ እና ተጨማሪ ኃይል ሰጪ ምግቦችን በትንሹ መጠን ቶሎ ቶሎ መውሰድ፣ አልኮል አለመጠጣት፣ ጨው መቀነስ፣ በሐኪም እስካልተከለከለ ድረስ በርከት ያለ ፈሳሽ መውሰድ፣ መጠነኛ የሆነ እንቅስቃሴ ማዘውተር እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ያስረዳሉ።