ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ጋር ትጫወታለች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለ36ኛው የአፍሪካ  ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ከሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ጋር ዛሬ ታደርጋለች።

የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ በሞሮኮ ኤል አብዲ ስታዲየም ምሽት 12 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።

36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እ.አ.አ ጁን 2027 በኬንያ ፣ ዩጋንዳና ታንዛንያ ጣምራ አዘጋጅነት ይከናወናል።

በአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ 12 አገራት የደርሶ መልስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ከጨዋታዎቹ መካከል ኢትዮጵያ ከሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ጋር የምታደርገው ይገኝበታል።

የሁለቱ ሀገራት የመጀመሪያ ጨዋታ ዛሬ ይካሄዳል።

ብሄራዊ ቡድኖቹ በውድድር ጨዋታዎች ሲገናኙ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።

ከዚህ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች በተመሳሳይ አንድ ጊዜ አሸንፈዋል።

ሩሲያ እ.አ.አ በ2018 ባዘጋጀቸው 21ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ ላይ ተገናኝተው ኢትዮጵያ በድምር ውጤት 3 ለ 1 በማሸነፍ ቀጣዩን ዙር መቀላቀሏ የሚታወስ ነው።

በመጀመሪያው ጨዋታ ሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ 1 ለ 0 ስታሸንፍ ኢትዮጵያ በመልሱ ጨዋታ 3 ለ 0 አሸንፋለች።

 

ዮሐንስ ሳህሌ በታህሳስ ወር 2018 ዓ.ም በሁለት ዓመታት የውል ጊዜ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው በይፋ መሾማቸው ይታወቃል።

አዲሱ አሰልጣኝ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ዛሬ ያደርጋሉ።

አሰልጣኝ ዮሐንስ ለጨዋታዎቹ ጥሪ ያደረጉላቸው ተጫዋቾች ለስምንት ቀናት በአዲስ አበባ ልምምዳቸውን አድርገዋል።

ብሄራዊ ቡድኑ የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት ማምሻውን በኤል አብዲ ስታዲየም ማድረጉን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

በ47 ዓመቱ ፓርቹጋላዊ ሪካርዶ ሞናሳንቶ የሚመራው የሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ብሄራዊ ቡድን ለጨዋታ ለአንድ ሳምንት ያህል ልምምዱን አከናውኗል።

በፊፋ ወርሃዊ የሀገራት የእግር ኳስ ደረጃ ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ 189ኛ ደረጃን ይዛለች። ኢትዮጵያ 147ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች የመልስ ጨዋታቸውን መጋቢት 22 ቀን 2018 ዓ.ም በድሬዳዋ ስታዲየም ያደርጋሉ።

በደርሶ መልስ የሚያሸንፈው ሀገር ወደ ምድብ ድልድል ምዕራፍ ማለፉን ያረጋግጣል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም