ቀጥታ፡

23ኛው ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድር እና 19ኛው የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል በሐረር ከተማ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2018 (ኢዜአ)፦  23ኛው ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድር እና 19ኛው የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል ከመጋቢት 20 እስከ 27 ቀን 2018 ዓ.ም በሐረር ከተማ እንደሚካሄድ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድ ውድድሩንና ፌስቲቫሉን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው መንግስት ለስፖርት ልማት በሰጠው ልዩ ትኩረት በአዲሱ የስፖርት ፖሊሲ አማካኝነት የባህል ስፖርቶችን ለማልማት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሁነቱ  የኢትዮጵያን ህብረ ብሄራዊ አንድነት፣ ብዝሃነት እና አብሮነት የሚተዋወቅበት መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ባህል ስፖርት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ህይወት መሐመድ በበኩላቸው ውድድሩና ፌስቲቫሉ ህብረተሰቡን በባህል ስፖርት ተሳታፊና ተጠቃሚ ከማድረግም ባሻገር የባህል ስፖርትን ማህበረሰብ አቀፍ የማድረግ አላማ እንዳለው ገልጸዋል። 

በውድድርና ፌስቲቫሉ ከአፍሪካ ባህል ስፖርቶች እና ጨዋታዎች ኮንፌዴሬሽን የተጋበዙ የክብር እንግዶች እንደሚታደሙበት ጠቁመዋል።

በ11 የስፖርት አይነት በሚካሄደው ውድድርና ፌስቲቫል ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ1500 በላይ ስፖርተኞች ይሳተፋሉ።

ሁነቱ የኢትዮጵያ ባህል ስፖርት ፌዴሬሽን ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው።

ውድድሩና ፌስቲቫሉ "የባህል ስፖርቶች ልማት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚካሄድ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም