ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እያደረገች ላለው ብርቱ ጥረት እውቅና ልሰጥ እወዳለሁ-ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዌላ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤መጋቢት 17/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እያደረገች ላለው ብርቱ ጥረት እውቅና እንደሚሰጡ የድርጅቱ ዳይሬክተር ጀነራል ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዌላ (ዶ/ር) ገለጹ።

14ኛው የዓለም የንግድ ድርጅት (WTO) የሚኒስትሮች ስብሰባ (MC14) ዛሬ በካሜሮን ያውንዴ ይካሄዳል።

በሚኒስትሮች ስብሰባው ላይ የድርጅቱ 166 አባል ሀገራት የንግድ ሚኒስትሮች እና ከፍተኛ አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።

በንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) የተመራው ልዑክ በስብሰባው ላይ እየተሳተፈ ነው።

የዓለም ንግድ ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራል ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዌላ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር 22 ሀገራት የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

አንዳንድ ሀገራት አባል ለመሆን ለአስርት ዓመታት ጥረት ማድረጋቸውንና ሌሎች ሀገራት በቅርቡ ጥያቄያቸውን ማቅረባቸውን አመልክተዋል።

ከ22 ሀገራት በተጨማሪ የፋሮ ደሴቶች አባል ለመሆን ጥያቄ ያቀረበች አዲስ ሀገር መሆኗን ጠቁመው፥ጥያቄው ለድርጅቱ አጠቃላይ ምክር ቤት ገና አለመታየቱን ጠቁመዋል።

የዓለም ንግድ ድርጅት አባል የመሆን አድካሚ፣ብርቱ ጥረት እና ጽናት የሚጠይቅ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ አባል ለመሆን እየጣሩ ያሉ ሀገራት ለጠንካራ ስራቸው እና ትዕግስታቸው እውቅና መስጠት እወዳለሁ ብለዋል።

ዳይሬክተ ጀነራሏ ባደረጉት ንግግር በሚያደርጉበት ወቅት በስብሰባው ላይ እየተሳተፈ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ልዑክ እውቅና ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ እና ኡዝቤኪስታን እ.አ.አ በ2026 የድርጅቱ አባል እንደሚሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል ዋና ዳይሬክተሯ።

14ኛው የዓለም የንግድ ድርጅት (WTO) የሚኒስትሮች ስብስባ (MC14) እስከ መጋቢት 20 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

በንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) የተመራው ልዑክ ከስብሰባው ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት እና ተቋማት ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን እያደረጉ ይገኛል።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2026 የዓለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ድርድር ለማጠናቀቅ አቅዳ እየሰራች ትገኛለች።

የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሂደት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የደረሰ ሲሆን 7ኛው የስራ ቡድን ስብሰባ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ እ.ኤ.አ በኤፕሪል ወር 2026 ለማካሄድ ኢትዮጵያ ዝግጅቷን አጠናቃለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም