ዩኒቨርስቲው የጤናውን ዘርፍ ለማዘመን በሚደረገው ጥረት ብቁ የሰው ሃይልን በማፍራት ረገድ የድርሻውን እየተወጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርስቲው የጤናውን ዘርፍ ለማዘመን በሚደረገው ጥረት ብቁ የሰው ሃይልን በማፍራት ረገድ የድርሻውን እየተወጣ ነው
ደሴ፤ መጋቢት 17/2018(ኢዜአ)፦ ወሎ ዩኒቨርስቲ የጤናውን ዘርፍ ለማዘመን በሚደረገው ጥረት ብቁ የሰው ሃይልን በማፍራት የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት አወል ሰይድ (ዶ/ር) ገለፁ።
ዩኒቨርሲቲው "ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የሕክምና ትምህርትንና የመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤን ማሻሻል" በሚል መሪ ሀሳብ 2ኛውን ዓለም አቀፍ የጤና ምርምር ኮንፈረንስ እያካሄደ ነው።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አወል ሰይድ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ የጤናውን ዘርፍ ለማዘመን በሚደረገው ጥረት ተግባር ተኮር ትምህርት በመስጠት ብቁ ባለሙያዎች ማፍራት ላይ እየሰራ ነው።
የጤና ተቋማትን በግብዓት በመደገፍ፣ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማካሄድ ህብረተሰቡ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ የበኩሉን መወጣቱን አመልክተዋል።
የዛሬው ኮንፈረንስ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚደረጉ የምርምር ስራዎችን በውይይት በሚገኝ ግብዓት በማዳበር ወደ ተግባር ለማሸጋገር መካሄዱን አንስተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የልዕለ ሕክምና ካምፓስ ችፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር መታደል አዳነ (ዶ/ር) በበኩላቸው የህክምናውን ዘርፍ ከአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ጋር በማስተሳሰር የፈውስ ምጣኔን ለማሳደግ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በጤና ዘርፉ የሚሰሩ ምርምሮችን በቴክኖሎጂ ተደግፎ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሕክምና ትምህርት ቤት መምህር እና ተመራማሪ ዶክተር ዳዊት ወንድማገኝ ናቸው።
ሀገር በቀል እውቀቶችን ከዘመናዊ ትምህርት ጋር በማስተሳሰርና የሌሎች አገራትን ተሞክሮ በመቀመር የህክምናውን ዘርፍ ለማዘመን በሚደረጉ ተግባራት ዩኒቨርሲቲዎች ድርሻቸው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።
በጤና ሚኒስቴር የጤና ዘርፍ የሰው ሀብት ልማት ማሻሻያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሰግድ ሳሙኤል በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር፣ ቴክኖሎጂን በማላመድና በማስፋት የጤናውን ዘርፍ ማዘመን ላይ አተኩረው እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የጤና ተቋማትን ለማዘመንና የህክምና አገልግሎት ጥራትን ለማረጋገጥ በፓይለንት ደረጃ በተመረጡ የጤና ተቋማት የተጀመረውን ስራ ለማስፋት እንደሚሰራ አስረድተዋል።
ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመስጠት እየተደረገ ባለው ጥረት የዩኒቨርሲቲዎች ሚና ከፍ ያለ በመሆኑ ሚኒስቴሩ ተገቢውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል።
ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ኮንፈረንስ ላይም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን፣ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ አመራሮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።