ቀጥታ፡

በምዕራብ ሸዋ ዞን የፍራፍሬ ልማትን የማስፋፋት ስራ በትኩረት እየተከናወነ ነው

አምቦ፤ መጋቢት 17/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን የፍራፍሬ ልማትን የማስፋፋት ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ።

በዞኑ ቶኬ ኩታዬ ወረዳ የዞኑና የወረዳው አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው ማኅበረሰብ በተሳተፉበት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር፣ በ32 ሄክታር መሬት ላይ የሙዝ ችግኝ ተከላ ተጀምሯል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታ እንደገለጹት፤ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የፍራፍሬ ምርትን በቴክኖሎጂ በማስደገፍና አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በማቅረብ በሁሉም የዞኑ ወረዳዎች ሰፋፊ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

የፍራፍሬ ልማቱ በክረምት ዝናብ ብቻ ሳይወሰን በበጋ መስኖም ጭምር በስፋት እየተተገበረ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በዚህ ዓመትም በበጋ መስኖ ወደ 16 ሚሊዮን የሚጠጋ የሙዝ ችግኝ ለመትከል ታቅዶ፣ እስካሁን በተከናወነው ሥራም ከ100 ሺህ በላይ የሙዝ ችግኝ በ63 ሄክታር መሬት ላይ መተከሉን አስረድተዋል።

የቶኬ ኩታዬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዋዬሳ አላሙ በበኩላቸው፤ በበጀት ዓመቱ በበጋ መስኖ 472 ሄክታር መሬት በሙዝ ምርት ለመሸፈን መታቀዱን ገልጸዋል። 

የእስካሁኑን ሂደት ከተመለከትን አበረታች ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዕቅዱን ለማሳካት ከወረዳውና ከዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤቶች ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የወረዳው አርሶ አደሮች፤ በሙዝ ልማት ላይ ለመሳተፍ የሚያስችል ግንዛቤ ከግብርና ጽሕፈት ቤት ማግኘታቸውንና ከጥራጥሬ ሰብሎች ጎን ለጎን ሙዝ ማልማት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር ደረጄ ገላልቻ፤ ቀደም ሲል በአካባቢያቸው የሙዝ ምርት ብዙም ያልተለመደ ቢሆንም፣ አሁን ግን ከባለሙያዎች ባገኙት ሥልጠና መሠረት ከሌሎች ሰብሎች በተጨማሪ ፍራፍሬዎችን ለማምረት ማቀዳቸውን ገልጸዋል።

ሌላው አርሶ አደር ወይዘሮ ዳዊ ጉተታ በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ያመርቱ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ግን መንግሥት ባመቻቸው ዕድል በመጠቀም በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ሙዝን በክላስተር በማልማት በዓመት ሁለት ጊዜ ለማምረት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም