ቀጥታ፡

ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በ11ኛው የአፍሪካ፣ካሪቢያንና ፓሲፊክ ሀገራት ድርጅት የመሪዎች ጉባኤ ይሳተፋሉ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 17/2018 (ኢዜአ)፡-የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በ11ኛው የአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓሲፊክ ሀገራት ድርጅት የመሪዎች ጉባኤ ለመሳተፍ ማላቦ ኢኳቶሪያል ጊኒ ገብተዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ማላቡ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የኢኳቶሪያል ጊኒ ጠቅላይ ሚኒስትር ማኑዌል ኡሳ ኡዙዌን ጨምሮ የሀገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የአፍሪካ፣ካሪቢያንና ፓሲፊክ ሀገራት ድርጅት ከ5 አስርት አመታት በፊት እ.አ.አ በ1975 በቶጎ በተካሄደው ሎሜ ኮንቬንሽን ነበር የተጠነሰሰው፡፡

በሰኔ ወር በዚያው ዓመት ደግሞ ከአፍሪካ፣ካርቢያን እና ፓሲፊክ የተወጣጡ 46 ሀገራት በፈረሙት የጆርጅታውን ስምምነት መሰረት ድርጅቱ ተመስርቷል።

በተለያዩ የታሪክ ምዕራፎች ያለፈው ድርጅቱ አሁን ላይ 79 ሀገራትን በአባልነት ማካተት የቻለ ሲሆን የተፅዕኖ ደረጃውም በዚያው ልክ እያደገ ነው የመጣው።

ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ከንግድ እና ኢኮኖሚ ትብብር በተጨማሪ የልማት ፣ዴፕሎማሲ፣ ፖለቲካዊ እና አለም አቀፍ የፍትህ ጉዳዮች የሚንሸራሸሩበት መድረክ እየሆነ መጥቷል።

11ኛው የአፍሪካ፣ካሪቢያን እና ፓስፊክ ሀገራት ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ከመጋቢት 18- 20 / 2018 ድረስ የሚቆይ ይሆናል።

በጉባኤው ከሶስቱም ክልሎች የሚገኙ የሀገራት መሪዎች እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት እና የአውሮፓ ህብረት ተወካዮች እንደሚገኙ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም