ቀጥታ፡

ባህላዊ የግጭት አፈታት የፍትሕ ሥርዓቶች ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ጉልህ ፋይዳ እያበረከቱ ነው 

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2018 (ኢዜአ)፦ የዜጎች ባህላዊ የግጭት አፈታት የፍትሕ ሥርዓቶች ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ጉልህ ፋይዳ እያበረከቱ እንደሚገኝ የፍትሕ ሚኒስትር ሃና አርዓያስላሴ ገለጹ።

ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ዕውቅና በተሰጣቸው ባህላዊ የፍትሕና የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች ከሶስት ሚልየን በላይ ጉዳዮች መስተናገዳቸውን ተናግረዋል።

''በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የፍትሕ ተደራሽነት ለማረጋገጥ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስልቶችን ማጠናከር" በሚል መሪ ሃሳብ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የፍትሕ ተደራሽነት በአፍሪካ-2026 ጉባኤ ተጠናቋል።

በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ የተካሄደው ጉባኤ የአፍሪካን ባህላዊ የማህበረሰብ የፍትሕ ሥርዓቶችን ከመደበኛው የሕግ ማዕቀፍ ጋር ለማቀናጀት ልምድና ተሞክሮ ለመለዋወጥ ያለመ መድረክ መሆኑ ተገልጿል።

በባህላዊ የክርክር መፍቻ ሥርዓቶች ውስጥም የሥርዓተ ፆታ እኩልነትና የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃን በማሳደግ አስተማማኝ የፋይናንስ ሥርዓት ማፈላለግም ሌላኛው የጉባኤው ዓላማ መሆኑ ተመላክቷል።

የፍትሕ ሚኒስትር ሃና አርዓያስላሴ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የግጭት መፍቻ ባህላዊ ዕሴቶች መደበኛ የፍትሕ ሥርዓቱን በማገዝ ለሕግ የበላይነት መከበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል ተግባራዊ የተደረገው ባህላዊ ፍርድ ቤት ሌሎች ክልሎችም እንደየማህበረሰቡ ዕሴትና ሥርዓት ዕውቅና አግኝቶ ወደሥራ እየገባ እንደሚገኝ አንሰተዋል።

በቀጣይም ባህላዊ የግጭት መፍቻ የዳኝነት ዕሴቶችን በሁሉም ክልሎች ተደራሽ በማድረግ የማህበረሰብ አብሮነትና አንድነት ለማጎልበት በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

ለዚህም የክልሎችን ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት ለማስፋት በሚደረገው ጥረት ቀጣይነት ያለው ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ አንስተዋል።

በማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ቅቡልነት ያላቸው ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓቶችም ለዜጎች አፋጣኝ የፍትሕ ምላሽ በመስጠት ለዘላቂ ሰላምና እርቅ ገንቢ ሚና እየተወጡ መሆኑን አስረድተዋል። 

በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታትም በኢትዮጵያ ዕውቅና የተሰጣቸው የግጭት መፍቻ የማህበረሰብ ዕሴቶች ከሶስት ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ጉዳዮች መስተናገዳቸውን አስረድተዋል።

በጉባኤውም የአፍሪካዊያንን ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዕሴቶች ከመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት ጋር ለማናበብ መፍትሔ አመላካች ልምድና ተሞክሮዎች እንደተገኙበት ተናግረዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም