በክልሉ ሰላምን ለማዝለቅና ልማትን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ሚናውን ሊያጠናክር እንደሚገባ ተመላከተ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ሰላምን ለማዝለቅና ልማትን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ሚናውን ሊያጠናክር እንደሚገባ ተመላከተ
ወልዲያ፤ መጋቢት 17/2018( ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ሰላምን ለማዝለቅና ልማትን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ሚናውን ሊያጠናክር እንደሚገባ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ገለጹ።
በወልዲያ ከተማ በሠላምና ልማት ዙሪያ ከነዋሪዎች ጋር የምክክር መድረክ ዛሬ ተካሄዷል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የህዝቡ የነቃ ተሳትፎና ትብብር ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።
ለዚህም በክልሉ ሰላምን ለማዝለቅና ልማትን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ እየተወጣ ያለውን ሚና ሊያጠናክር እንደሚገባም አመልክተዋል።
የወልዲያ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ በበኩላቸው፤ ጽንፈኛው ቡድን በህዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ በመታገል እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የውይይት መድረኩም ይህን ተግባር ለማጠናከርና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት ደረጃ በደረጃ ለመፍታት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ ለሠላም መደፍረስ መነሻ የሆኑ ሀሰተኛ የማህበራዊ ሚዲያ ወሬዎችን ለይቶ መዋጋት አለበት ያሉት ደግሞ የመድረኩ ተሳታፊ ያሲን አሰፋ ናቸው።
በከተማ አስተዳደሩ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች የሚደነቁ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይህን ለማዝለቅም እያከናወንን ያለነውን ተግባር እናጠናክራለን ብለዋል።
የዘላቂ ሠላም ግንባታ ተግባር ለመንግስት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ የገለፁት ደግሞ ሌላኛው ተሳታፊ መሐመድ አሚን ናቸው።
ለአፍራሽ ሚዲያዎችና ለአላማ ቢስ ትግል ጆሮ ባለመስጠት ዘላቂ ሰላምን እውን በማድረግ የአካባቢያቸውን ልማት ለማፋጠን በሚደረገው ትግል የድርሻቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።
በመድረኩም የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች ተሳታፊ ሆነዋል።