ቀጥታ፡

የበልግ ዝናብ ስርጭት ለግብርና ምርታማነትና ለእንስሳት መኖ አቅርቦት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ነው-የኢትዮጵያ ሚትዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2018(ኢዜአ)፦የዘንድሮው የበልግ ዝናብ ስርጭት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚከናወኑ የግብርና ስራዎች ስኬታማነትና ለእንስሳት መኖ አቅርቦት መሻሻል ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር የኢትዮጵያ ሚትዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢንስቲትዩቱ የትንበያ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሳምነው ተሾመ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ፤ ተቋሙ የአየር ጸባይ አዝማሚያዎችን፣አዎንታዊና አሉታዊ ተጽዕኖዎችን በወቅቱ ለማህበረሰቡና ለሚመለከታቸው ተቋማት የማድረስ ስራውን በልዩ ትኩረት እየከወነ ይገኛል።

ከየካቲት እስከ ግንቦት ባለው የበልግ ወቅትም፣ በተለይም በሀገሪቱ ደቡባዊ አጋማሽ የዓመታዊ ዝናብ መጠኑ እስከ 55 በመቶ የሚሸፈንበት ዋነኛ ወቅት ነው ብለዋል።

በ2018 ዓ.ም የበልግ ወቅት አብዛኞቹ የአገሪቱ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡

እስካሁንም በ55 የሚደርሱ አካባቢዎች በ24 ሰዓት ውስጥ ከ35 እስከ 148 ሚሊ ሜትር የሚደርስ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ መመዝገቡን ገልጸዋል።

ባለፉት ቀናት የታየው ተስፋ ሰጪ የዝናብ ስርጭት ለአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት ጠቅሰው፥ ለበልግ እርሻ ዝግጅትና ለዘር ስራ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩንም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ለሰውና ለእንስሳት የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ማሻሻሉን እንዲሁም የእንስሳት መኖ ልማትን በማፋጠን ረገድ ከፍተኛ ድርሻ መኖሩ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

በመጪዎቹ ሚያዝያና ግንቦት ወራትም በደቡብ፣ በደቡብ ምዕራብ፣ በመካከለኛውና በሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች የበልግ ዝናብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በተለይም በደቡብና በደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ዝናቡ ዘግይቶ የሚወጣ በመሆኑ ለግብርናውና ለአካባቢ ጥበቃ ስራው ተጨማሪ ዕድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ወደ ጎርፍ አደጋ ሊቀየር ስለሚችል ማህበረሰቡና የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም