ቀጥታ፡

ድሬዳዋ ከተማ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማ አርባምንጭ ከተማን 1 ለ 0 አሸንፏል።

በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ የአርባምንጭ ከተማዋ መድሃኒት ዓለሙ በ79ኛው ደቂቃ በራሷ ላይ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥራለች። 

የድሬዳዋ ከተማዋ መዓዛ አብደላ የጨዋታው ኮከብ በመባል ተመርጣለች። 

ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ድሬዳዋ ከተማ በ24 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል። በሊጉ ሰባተኛ ድሉንም አስመዝግቧል።

በውድድር ዓመቱ 15ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው አርባምንጭ ከተማ በ10 ነጥብ የመጨረሻውን 10ኛ ደረጃን ይዟል።

አርባምንጭ ከተማ ባለፉት 14 የሊጉ ጨዋታዎች አላሸነፈም። 

ዛሬ አስቀድመው በተደረጉ ጨዋታዎች ይርጋጨፌ ቡና አዲስ አበባ ከተማን 4 ለ 2፣ ቦሌ ክፍለ ከተማ ባህር ዳር ከተማን 2 ለ 0 አሸንፈዋል።

ጨዋታዎቹን ተከትሎ 21ኛ ሳምንት ተጠናቋል። 

የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከመጋቢት 28 እስከ ሚያዚያ 10 ቀን 2018 ዓ.ም በቱርክዬ በሚከናወነው የዩኤፋ የወዳጅነት ዋንጫ ዝግጅት እና ተሳትፎ ያደርጋል። 

በብሔራዊ ቡድኑ ተሳትፎ ምክንያት የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ እንደሚቋረጥ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም