ቀጥታ፡

የሹዋሊድ ምሽት ሐረር እንደ ጨረቃና እንደ ከዋክብት በሐረሪዎች ውብ ባህል፣ በልዩ ዜማና ትዕይንት የምትደምቅበት ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ ፤ መጋቢት 17 /2018 ( ኢዜአ)፦የሹዋሊድ ምሽት ሐረር እንደ ጨረቃና እንደ ከዋክብት በሐረሪዎች ውብ ባህል፣ በልዩ ዜማና ትዕይንት የምትደምቅበት ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እንኳን ለሹዋሊድ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የሹዋሊድ ምሽት ሐረር እንደ ጨረቃና እንደ ከዋክብት በሐረሪዎች ውብ ባህል፣ በልዩ ዜማና ትዕይንት የምትደምቅበት ነው። በዓሉ ከባህላዊ ሥነ ሥርዓትነቱ ባለፈ፣ የጥንታዊቷ ጀጎል የታሪክ ዐሻራ፣ የሕዝቦች የአብሮነት መድረክና የኢትዮጵያ የባህል ብዝኃነት ማሳያ ነው።


 

ሹዋሊድ የማኅበራዊ ትሥሥር ድልድይ ነው። ቂም በቀል የሚሻርበት፣ በወጣቱና በአረጋውያን መካከል ያለው የትውልድ ሠንሰለት በምርቃትና በምክር የሚታደስበት፣ እንዲሁም የአብሮነትና የመቻቻል ዕሴቶቻችን በደመቀ ሁኔታ የሚታዩበት ልዩ ዓመታዊ ክብረ በዓል ነው።

መንግሥታችን ለሀገራዊ ቅርሶችና ለቱባ ባህላዊ እሴቶች ጥበቃ ልዩ ትኩረት የሰጠው፣ እንደ ሹዋሊድ ያሉ ቅርሶቻችን የቱሪስት መስሕብና የሀገራዊ አንድነታችን ምሰሶ ሆነው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ነው።


 

በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ ጭምር ዕውቅናን ያገኘው ሹዋሊድ፣ የሐረርን ብቻ ሳይሆን የሁላችንንም እንግዳ ተቀባይነትና የከበረ ዕሴት ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ሚና አለው።

በድጋሚ ለሐረሪ ሕዝብና ለከተማዋ ነዋሪዎች በሙሉ እንኳን ለሹዋሊድ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል።

#Ethiopian_News_Agency

#ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም